ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ተግሣጽ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጠል በመከር ዝናምም በበጋ ጥቅም እንደሌለው፥ እንዲሁ ለሰነፍ ክብር አይገባውም። 2 እንደሚተላለፍ ድንቢጥ፥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ ርግማን በማንም ላይ አይደርስም። 3 አለንጋ ለፈረስ፥ መውጊያ ለአህያ እንደ ሆነ፥ እንደዚሁም በትር ለሰነፍ ጀርባ ነው። 4 ልጄ ሆይ፥ አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል፥ ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት። 5 ነገር ግን ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው፥ ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት። 6 በሰነፍ መልእክተኛ እጅ ነገርን የሚልክ፥ በእግሮቹ ውርደትን ያመጣል። 7 የአንካሳ እግሮች አካሄድ ልዩ ነው፥ እንዲሁም በደል በሰነፎች አፍ ነው። 8 ለሰነፍ ክብርን የሚሰጥ ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው። 9 እሾህ በሰካራም እጅ እንደሚሰካ፥ እንዲሁም መገዛት በሰነፎች እጅ ነው። 10 የአላዋቂ ሰውነት ሁሉ ብዙ ይታወካል፥ ዐሳቡ ይበታተናልና። 11 ወደ ትፋቱ የሚመለስ ውሻ የተጠላ እንደሆነ በክፋቱ ወደ ኀጢአቱ የሚመለስ አላዋቂም እንዲሁ ነው። ኀጢአትን የምታመጣ ኀፍረት አለች፤ ክብርንና ጸጋን የሚያመጣ ኀፍረትም አለ። 12 ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚመስለውን ሰው አየሁ፥ ከእርሱ ይልቅ ለአላዋቂ እጅግ ተስፋ አለው። 13 ታካች ሰው በላኩት ጊዜ፥ “አንበሳ በመንገድ አለ፤ በሜዳም ገዳዮች አሉ” ይላል። 14 ሣንቃ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፥ እንዲሁ ታካች ሰው በአልጋው ላይ ይመላለሳል። 15 ታካች ሰው እጁን በብብቱ ይሸሽጋል፤ ወደ አፉም ይመልሳት ዘንድ ለእርሱ ድካም ነው። 16 ታካች ሰው መልእክትን በአጥጋቢ ሁኔታ ከሚመልስ ሰው ይልቅ፥ ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል። 17 አልፎ በሌላው ጥል የሚደባለቅ፥ የውሻን ጅራት እንደሚይዝ ነው። 18 ይድኑ ዘንድ የሚወድዱ ለሰው ነገርን እንደሚያወጡ እንደዚሁ ነገርን የሚቀበል አስቀድሞ ይወድቃል፥ 19 ባልንጀራቸውን የሚያታልሉ ሁሉ እንደዚሁ ናቸው፤ ካወቁባቸውም በኋላ በጨዋታ አደረግነው ይላሉ። 20 በዕንጨት መታጣት እሳት ይጠፋል፥ በዕንጨት ብዛትም እሳት ይነድዳል፥ ቍጡ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል። 21 ከሰል ፍምን፥ ዕንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥ እንዲሁ ተሳዳቢ ሰው ለጠብና ለክርክር ነው። 22 የአታላዮች ቃል ደካማ ነው፥ ነገር ግን የምሕረት መዝገቦችን ይሰብራል። 23 በሐሰት የሚሰጥ ብር እንደ ገል ነው፥ በሸክላ ዕቃ ላይ የሚለበጥ ብር ግብዝ እንደ ሆነ እንደዚሁም ልዝቦች ከንፈሮች ያዘነች ልብን ይሸፍናሉ። 24 ጠላት እያለቀሰ በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥ በልቡ ግን ተንኮልን ያኖራል። 25 ጠላትህ በታላቅ ድምፅ ደስ ቢያሰኝህ አትመነው፥ በልቡ ሰባት ክፋቶች አሉበትና። 26 ጠላትነቱን የሚሸሽግ ተንኰልን ይሰበስባል፥ ዐዋቂ ግን በጉባኤ መካከል በደሉን ይገልጣል። 27 ጕድጓድን ለባልንጀራው የሚምስ ራሱ ይወድቅበታል፥ ድንጋይንም የሚያንከባልል በላዩ ይገለበጥበታል። 28 ሐሰተኛ ምላስ እውነትን ትጠላለች፥ ዝም የማይል አፍም ክርክርን ያመጣል። |