መዝሙር 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ በሙት ላቤን የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ ታምራትህንም ሁሉ እናገራለሁ። 2 በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ። 3 ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው በተመለሱ ጊዜ፥ ይታመሙ፥ ከፊትህም ይጥፉ። 4 ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ የጽድቅ ፈራጅ ሆይ፥ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ። 5 አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችም ጠፉ፥ ስማቸውንም ለዘለዓለም ደመሰስህ። 6 ጠላቶች በጦር ለዘለዓለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውንም በአንድነት ታጠፋለህ። 7 እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፤ 8 እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይዳኛታል። አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል። 9 እግዚአብሔርም ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው። 10 ስምህን የሚወዱ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና። 11 በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን ንገሩ፤ 12 ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና። 13 አቤቱ፥ ይቅር በለኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የሚያደርገኝ፤ 14 ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፤ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ፥ በማዳንህ ደስ ይለናል። 15 አሕዛብ በሠሩት በደላቸው ጠፉ፥ በዚያችም በሸሸጓት ወጥመድ እግራቸው ተጠመደ። 16 እግዚአብሔር ፍርድን ማድረግ ያውቃል፤ ኀጢአተኛው በእጆቹ ሥራ ተጠመደ። 17 ኀጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሱ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ። 18 ድሃ ለዘለዓለም የሚረሳ አይደለምና፥ ችግረኞችም ተስፋቸውን ለዘለዓለም አያጡም። 19 አቤቱ፥ ተነሥ፥ ሰውም አይበርታ፥ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው። 20 አቤቱ፥ የሕግ መምህርን በላያቸው ላይ ሹም፤ አሕዛብም ሰዎች እንደ ሆኑ ይወቁ። 21 አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ቸል ትላለህ? 22 በኀጢአተኛ ትዕቢት ድሃ ይናደዳል፤ ባሰቡት ተንኮላቸው ይጠመዳሉ። 23 ኀጢአተኛ በነፍሱ ፈቃድ ይወደሳል፥ ዐመፀኛም ይባረካል። 24 ኀጢአተኛ እግዚአብሔርን አበሳጨው፥ እንደ ቍጣውም ብዛት አይመራመረውም፤ በእርሱ ፊት እግዚአብሔር የለም። 25 መንገዱ ሁሉ የረከሰ ነው፥ ፍርድህም በፊቱ የፈረሰ ነው፥ ጠላቶቹንም ሁሉ ይገዛቸዋል። 26 በልቡ ይላል፥ “ለልጅ ልጅ አልታወክም ክፉም አያገኘኝም።” 27 አፉ መርገምንና ሽንገላን የተመላ ነው፤ ከምላሱ በታች ድካምና መከራ ነው። 28 ከባለጸጎች ጋር ይሸምቃል፥ ያድድናልም ንጹሑን በስውር ይገድል ዘንድ፥ ዐይኖቹም ወደ ድሃው ይመለከታሉ። 29 እንደ አንበሳ በጕድጓድ በስውር ይሸምቃል፤ ድሃውን ለመንጠቅ ያደባል፤ ድሃውን ይነጥቀዋል፥ ይስበዋልም። 30 በወጥመዱም ያዋርደዋል፥ ይጐብጣል፥ ድሃውንም በገዛው ጊዜ ይወድቃል። 31 በልቡም ይላል፥ “እግዚአብሔር ረስቶኛል፤ ፈጽሞም እንዳያይ ፊቱን መለሰ።” 32 አቤቱ፥ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ፥ እጅህም ከፍ ከፍ ትበል፤ ድሆችንም አትርሳ። 33 ኀጢአተኛ ስለ ምን እግዚአብሔርን አስቈጣው? በልቡ፥ “አይመራመረኝም” ይላልና። 34 አንተ ድካምንና ቍጣን እንድትመለከት ታያለህን? በእጅህ አሳልፈህ እንድትሰጠው፥ እንግዲህ ድሃ በአንተ ላይ ተጣለን? ለድሃ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ? 35 የኀጢአተኛንና የክፉን ክንድ ስበር፥ ስለ እርሱም ኀጢአቱ ትመረመራለች፥ አትገኝምም። 36 እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይነግሣል፤ አሕዛብ ከምድር ይጠፋሉ። 37 እግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን ዐሳብ አደመጠች፥ 38 ፍርዱ ለድሃ አደግና ለችግረኛ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ አፋቸውን ከፍ ከፍ ማድረግን እንዳይደግሙ። |