Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)

1 በመኳንንት ማዕድ ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥ ያቀረቡልህን ፈጽመህ ዕወቅ፤

2 በእጅህ ተቀበል፥ እንደዚህም ታዘጋጅ ዘንድ እንዳለህ ዕወቅ።

3 ብትሳሳ ግን ምግቡን አትውደድ እርሱ የሐሰት እንጀራ ነውና።

4 አንተም ድሃ ስትሆን ከባለጠጋ ጋር አትወዳደር። በዐሳብህም ራቅ።

5 በእርሱ ላይ ዐይንህን ብታተኩር አታገኘውም፥ ለእርሱ የንስር ክንፍ ተዘጋጅቶለታልና። ወደሚቆምበትም ቤት ይመለሳልና።

6 ከስስታም ሰው ጋር አትመገብ፥ ምግቡንም አትመኝ፤

7 ሣርን እንደሚበላ ይበላል፥ ይጠጣልም፤ ወደ አንተም አታስገባው፥ ከእርሱ ጋርም እንጀራን አትብላ፥ ብላ፥ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም።

8 የበላኸውን ትተፋለህ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋለህ።

9 በሰነፍ ጆሮ አንዳች አትናገር፥ የነገርህን ጥበብ እንዳይንቅብህ።

10 አባቶችህ ያኖሩትን የድንበር ምልክት አታፍልስ፤ ወደ ድሃ አደጎች እርሻም አትግባ፤

11 ታዳጊአቸው እግዚአብሔር ጽኑ ነውና፥ እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና።

12 ልብህን ለተግሣጽ ስጥ፥ ጆሮህንም ለዕውቀት ቃል አዘጋጅ።

13 ሕፃናትን ከመቅጣት ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታቸው አይሞቱምና።

14 አንተ በበትር ትመታቸዋለህ፥ ነፍሳቸውን ግን ከሞት ታድናለህ።

15 ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ይሁን ልቤን ደግሞ ደስ ያሰኛል፤

16 በከንፈሮችህ ቃሌ ብትኖር ለከንፈሮቼ የቀኑ ይሆናሉ።

17 ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፤

18 ብትጠብቃቸው ዘመድ ይሆኑሃል፥ ተስፋህም አትጠፋም።

19 ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ጠቢብም ሁን፥ የልብህንም ዐሳብ አቅና።

20 የወይን ጠጅ ጠጭ አትሁን፤ ለሥጋም አትሳሳ

21 ሰካራምና አመንዝራ ይደኸያል፥ እንቅልፋምም ሁሉ የተቦጫጨቀ ጨርቅ ይለብሳል።

22 ልጄ ሆይ፥ የወለደህን አባትህን ስማ፥ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።

23 እውነትን ግዛ፥ አትሽጣትም፥ ጥበብንና ተግሣጽን፥ ማስተዋልንም።

24 ጻድቅ አባት በመልካም ያሳድጋል፥ በብልህ ልጅም ነፍሱ ደስ ይላታል።

25 አባትህና እናትህ በአንተ ደስ ይላቸዋል፥ አንተንም የወለደች ደስ ይላታል።

26 ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዐይኖችህም መንገዴን ይጠብቁ።

27 አመንዝራ ሴት የተነደለች ማድጋ ናት፥ ሌላዪቱም ሴት የጠበበች ጕድጓድ ናት።

28 ወደ እርሷ የሄደ ፈጥኖ ይጠፋል፥ ጠማማ ሰውም ሁሉ ያልቃል።

29 ልጄ ሆይ፥ ዋይታ ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዐይን ቅላት ለማን ነው?

30 የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የወይንን ፍለጋ ለሚከተሉስ አይደለምን? ግብዣ ከተደረገ ዘንድ በወይን አትስከሩ፥ ነገር ግን ከደጋግ ሰዎች ጋር በመደማመጥ ተነጋገሩ።

31 ወደ ጽዋዎችና ወደ ብርሌ ዐይንህን ብትሰጥ፥ በኋላ እንደ ግንብ ዕራቁትህን ትሄዳለህ፤

32 በመጨረሻም እባብ እንደ ነደፈው፥ የእፉኝትም መርዝ እንደ ተሰራጨበት ትዘረጋለህ።

33 ዐይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ያንጊዜም አፍህ ጠማማ ነገርን ይናገራል።

34 በጥልቅ ባሕር ውስጥ እንደሚተኛ ትሆናለህ፥ በብዙ ማዕበል ውስጥም እንደሚቀዝፍ።

35 “መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፤ ዘበቱብኝ፥ እኔም አላወቅሁም። ከእኔ ጋር የሚሄዱትን መጥቼ እፈልግ ዘንድ መቼ ጧት ይሆናል?” ትላለህ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች