ሆሴዕ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጣዖት አምልኮ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 1 ካህናት ሆይ! ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! አድምጡ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ! ልብ አድርጉ፤ ለሚመለከት ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው። 2 የሚያድኑ አዳኞች ያጠምዱባት ዘንድ ተከሏት፤ እኔ ግን መካሪያችሁ ነኝ። 3 እኔ ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፤ እስራኤልም ከእኔ አልራቀም፤ ኤፍሬም ዛሬ አመንዝሮአልና፤ እስራኤልም ረክሶአልና። 4 ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ልባቸውን አላቀኑም፤ የዝሙት መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ እግዚአብሔርንም አላወቁትምና። 5 የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኀጢአታቸው ይደክማሉ፤ ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ይደክማል። 6 እግዚአብሔርንም ለመሻት ከበጎቻቸውና ከላሞቻቸው ጋር ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱ ተለይቶአልና አያገኙትም። 7 ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ከድተዋል፤ አሁንም ኵብኵባ እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል። ጦርነት በይሁዳና በእስራኤል መካከል 8 በኮረብታ ላይ መለከትን ንፉ፤ በተራሮችም ላይ ጩኹ፤ ብንያም በተዋረደበት በቤትአዌን ዐዋጅ ንገሩ። 9 ኤፍሬም በዘለፋ ቀን ለጥፋት ይሆናል፤ በእስራኤልም ነገዶች የታመነውን ነገር አሳየሁ። 10 የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚያፈርሱ ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ። 11 ኤፍሬም የተገፋ ሆነ፤ በፍርድም ተረገጠ፤ ከንቱን ይከተል ዘንድ ጀምሮአልና። 12 እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ እሆንበታለሁ። 13 ኤፍሬምም ደዌውን አያት፤ ይሁዳም ሥቃዩን አያት፤ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ፤ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ፈጽሞ ይፈውሳችሁ ዘንድ አልቻለም፤ ከእናንተም ሕማም አልተወገደም። 14 እኔም ለኤፍሬም እንደ ነብር፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ፤ እወስድማለሁ፤ የሚያድናቸውም የለም። 15 እስኪጠፉ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ እሄዳለሁ፤ ወደ ስፍራዬም እመለሳለሁ። |