ዘዳግም 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጋብቻና ፍች የተሰጠ ሕግ 1 “አንድ ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፤ ከቤቱም ይስደዳት። 2 ከቤቱም ከወጣች በኋላ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ 3 ሁለተኛውም ባል ቢጠላት፥ የፍችዋንም ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ቢሰጣት ፥ ከቤቱም ቢሰድዳት፥ ወይም ሚስት አድርጎ ያገባት ሁለተኛው ባልዋ ቢሞት፥ 4 የሰደዳት የቀድሞ ባልዋ ከረከሰች በኋላ ደግሞ ያገባት ዘንድ አይገባውም፤ ያ በእግዚአብሔር የተጠላ ነውና፤ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር አታርክስ። ልዩ ልዩ ሕግጋት 5 “አዲስ ሚስትም ያገባ ሰው ወደ ጦርነት አይሂድ፤ ምንም ነገር አይጫኑበት፤ ነገር ግን አንድ ዓመት በቤቱ በፈቃዱ ይቀመጥ፤ የወሰዳትንም ሚስቱን ደስ ያሰኛት። 6 “የሰውን ነፍስ እንደ መውሰድ ነውና ወፍጮ ወይም መጅ ስለ መያዣ ማንም አይውሰድ። 7 “ማንም ሰው ከእስራኤል ልጆች ከወንድሞቹ ሰውን አፍኖ ሲሰርቅና ሲሸጥ ቢገኝ ያን የሰረቀውን ሰው ይግደሉት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከላችሁ አርቁ። 8 “ስለ ለምጽ ደዌ ሌዋውያን ካህናት ያስተማሩህን ሁሉ ፈጽመህ እንድትጠብቅ እንድታደርግም ተጠንቀቅ፤ እኔ ያዘዝኋቸውን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። 9 አምላክህ እግዚአብሔር ከግብፅ ባወጣችሁ ጊዜ በመንገድ ሳላችሁ በማርያም ላይ ያደረገውን ዐስብ። 10 “ለባልንጀራህ ባበደርኸው ጊዜ መያዣውን ልትወስድ ወደ ቤቱ አትግባ። 11 አንተ ግን በውጭ ቁም፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ወደ ውጭ ያውጣልህ። 12 ያም ሰው ድሃ ቢሆን መያዣውን በአንተ ዘንድ አታሳድር። 13 ለብሶት እንዲተኛ እንዲባርክህም ፀሐይ ሳይገባ መያዣውን ፈጽመህ መልስለት፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ምጽዋት ይሆንልሃል። 14 “ከወንድሞችህ ወይም በሀገርህ ውስጥ ከአሉት መጻተኞች ድሃና ችግረኛ የሆነውን ምንደኛ ደመወዙን አትከልክለው፤ 15 ድሃ ነውና፥ ተስፋውም እርሱ ነውና ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኽብህ፥ ኀጢአትም እንዳይሆንብህ ደመወዙን ፀሐይ ሳይገባ በቀኑ ስጠው። 16 “አባቶች ስለ ልጆቻቸው አይገደሉ፤ ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኀጢአቱ ይገደል። 17 “የመጻተኛውንና የድሃ-አደጉን፥ የመበለቲቱንም ፍርድ አታጣምምባቸው፤ የመበለቲቱንም ልብስ ለመያዣ አትውሰድባት። 18 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ ዐስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ። 19 “የእርሻህን መከር ባጨድህ ጊዜ ነዶም ረስተህ በእርሻህ ብታስቀር፥ ትወስደው ዘንድ አትመለስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ፥ ለመጻተኛና ለድሃ-አደግ፥ ለመበለትም ተወው። 20 የወይራህን ፍሬ በለቀምህ ጊዜ ከቅርንጫፎቹ ላይ አጥርተህ ለመልቀም ዳግመኛ አትመለስ፤ ለመጻተኛና ለድሃ-አደግ፥ ለመበለትም ይሁን። 21 የወይንህን ፍሬ በቈረጥህ ጊዜ ቃርሚያውን አትልቀመው፤ ለመጻተኛና ለድሃ-አደግ፥ ለመበለትም ይሁን። 22 አንተም በግብፅ ሀገር መጻተኛ እንደ ነበርህ ዐስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ። |