Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 83 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእስራኤል ጠላቶች እንዲሸነፉ የቀረበ ጸሎት

1 አምላክ ሆይ! እባክህ ዝም አትበል፤ አትተወን፤ ችላ አትበል!

2 እነሆ፥ ጠላቶችህ ዐምፀዋል፤ የሚጠሉህ ሁሉ ራሳቸውን በአንተ ላይ አንሥተዋል።

3 በሕዝብህ ላይ በስውር ያደባሉ፤ አንተ በምትጠብቃቸው ላይ ያሤራሉ።

4 “እስራኤል ለዘለዓለም የተረሳ እንዲሆን ኑ፤ መንግሥታቸውን እንደምስስ” ይላሉ።

5 በአንድነት በአንተ ላይ አሤሩ፤ በአንተ ላይ ለመነሣት የቃል ኪዳን ስምምነት አደረጉ።

6 እነርሱም የኤዶም፥ የእስማኤል፥ የሞአብ፥ የአጋርያን፥

7 የጌባል፥ የዐሞን፥ የዐማሌቅ፥ የፍልስጥኤምና የጢሮስ ሰዎች ናቸው።

8 አሦርም የሎጥን ልጆች በመርዳት ከእነርሱ ጋር ተባብራለች።

9 በምድያማውያን፥ በሲሣራና በያቢንም ላይ በቂሾን ወንዝ ያደረግኸውን በእነዚህም ላይ አድርግ።

10 እነርሱን በዔንዶር ድል አደረግሃቸው፤ ሬሳቸውም በሜዳ ላይ በስብሶ ቀረ።

11 በዖሬብና በዜብ ላይ ያደረግኸውን በእነርሱም መሪዎች ላይ አድርግ፤ በዜባሕና በጻልሙናዕ ያደረግኸውን በእነርሱም ገዢዎች ላይ አድርግ።

12 እነርሱ “የእግዚአብሔርን ሕዝብ ርስት የራሳችን እናደርጋለን” ብለው ነበር።

13 ስለዚህ አምላኬ ሆይ! እንደ ትቢያ፥ በነፋስም እንደሚወሰድ ገለባ በትናቸው።

14 እሳት ደንን እንደሚያጋይ፥ የእሳት ነበልባልም ተራራዎችን እንደሚያቃጥል

15 በሞገድህ አባራቸው፤ በዐውሎ ነፋስህም አስደንግጣቸው።

16 እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ይሹ ዘንድ ፊታቸውን በኀፍረት ሸፍን፤

17 ዐፍረው ለዘለዓለም ተስፋ እንዲቈርጡ አድርግ፤ ተዋርደውም እንዲጠፉ አድርግ።

18 በምድር ሁሉ ላይ ጌታና ሁሉን ቻይ አምላክ አንተ እግዚአብሔር እንደ ሆንክ ይወቁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች