ሐዋርያት ሥራ 26 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጳውሎስ በአግሪጳ ፊት ያደረገው ንግግር 1 አግሪጳም ጳውሎስን “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል፤” አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2-3 “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። 4 “ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ 5 ሊመሰክሩ ይወዱ እንደሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና። 6 አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። 7 ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል ዐሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ከአይሁድ እከሰሳለሁ። 8 እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደሆነ ስለምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቆጠራል? 9 “እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። 10 ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፤ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። 11 በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቆጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር። ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ እንዴት እንደ ተመለሰ መተረኩ ( የሐዋ. 9፥1-19 ፤ 22፥6-16 ) 12 “ስለዚህም ነገር ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ 13 ንጉሥ ሆይ! በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤ 14 ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ ‘ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ለአንተ ይብስብሃል፤’ የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ። 15 እኔም ‘ጌታ ሆይ! ማን ነህ?’ አልሁ። እርሱም አለኝ ‘አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ። 16 ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። 17-18 የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዐይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።’ ጳውሎስ ስለ ሥራው ሁኔታ እንደ አስረዳ 19 “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። 20 ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሓ ይገቡ ዘንድና ለንስሓ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ተናገርሁ። 21 ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ሞከሩ። 22-23 ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።” ጳውሎስ ንጉሥ አግሪጳ እንዲያምን መማጸኑ 24 እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ “ጳውሎስ ሆይ! አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል፤” አለው። 25 ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ! የእውነትንና የአምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። 26 በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። 27 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።” 28 አግሪጳም ጳውሎስን “በጥቂት ጊዜ ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ፤” አለው። 29 ጳውሎስም “በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራት በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ፤” አለው። 30 ንጉሡም፥ አገረ ገዢውም፥ በርኒቄና ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፤ 31 ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ፤” ብለው ተነጋገሩ። 32 አግሪጳም ፈስጦስን “ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር፤” አለው። |