የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


ምሳሌ 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
ምሳሌ 12

1 ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፥ እርማትን የሚጠላ ግን ሞኝ ነው።

2 መልካም ሰው ከጌታ ዘንድ ሞገስን ያገኛል፥ ተንኰለኛውን ሰው ግን ጌታ ይፈርድበታል።

3 ክፋት ለሰው ዋስትና አያስገኝም፥ የጻድቃንን ሥር ግን ምንም አያንቀሳቅሰውም።

4 ጐበዝ ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፥ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት።

5 የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፥ የክፉዎች ምክር ግን ሽንገላ ነው።

6 የክፉ ሰዎች ቃላት ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ የቅኖች አፍ ግን ያድናቸዋል።

7 ክፉ ሰዎች ይወድቃሉ፥ ፈጽሞም አይገኙም፥ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።

8 ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፥ ልቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል።

9 ምግብ ሳይኖረው ከሚኮራ ሰው አገልጋይ ኖሮት የተዋረደ ሰው ይሻላል።

10 ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፥ የክፉ ሰው ርኅራኄ ግን ጭካኔ ነው።

11 መሬቱን የሚቆፍር ሰው እንጀራ ይጠግባል፥ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን ማስተዋል የተሣነው ነው።

12 ክፉ ሰዎች በክፉዎች ወጥመድ ይደሰታሉ፥ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል።

13 ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፥ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል።

14 የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል።

15 የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፥ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል።

16 የሰነፍ ቁጣ ቶሎ ይታወቃል፥ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል።

17 እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፥ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል።

18 እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፥ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።

19 የእውነት ከንፈር ለዘለዓለም ትቆማለች፥ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው።

20 ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፥ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው።

21 ጻድቅን መከራ አያገኘውም፥ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው።

22 ውሸተኛ ከንፈር በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።

23 ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፥ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል።

24 የትጉ እጅ ትገዛለች፥ የታካች እጅ ግን ትገብራለች።

25 ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፥ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።

26 ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፥ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች።

27 ታካች ሰው አደን ምንም አያድንም፥ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው።

28 በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ በጎዳናዋም ሞት የለም።