የወይን አትክልት ሠራተኞች ምሳሌ1 “መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ የአትክልት ቦታ ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ትመስላለችና። 2 ከሠራተኞቹ ጋር በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሰደዳቸው። 3 ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎችን አየ፤ 4 እነርሱንም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ፤’ አላቸው። 5 እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። 6 ወደ ዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ አላቸው። 7 እነርሱም ‘የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው፤’ አሉት። እርሱም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤’ አላቸው። 8 በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ ሹሙን ‘ሠራተኞቹን ጥራና ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። 9 ዐሥራ አንድ ሰዓት ላይ የገቡት መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 10 መጀመሪያ የመጡትም በቀረቡ ጊዜ የበለጠ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 11 በተቀበሉም ጊዜ በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ። 12 እንዲህም አሉት ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑን ድካምና ሐሩር ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው።’ 13 እርሱ ግን ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም፤ ከእኔ ጋር በአንድ ዲናር አልተስማማህምን? 14 የአንተ የሆነውን ውሰድና ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁህን ያህል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈለግሁ። 15 የራሴ በሆነ ነገር ላይ የወደድሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንኩ ትመቀኛለህን? 16 ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።’” ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለሦስተኛ ጊዜ እንደ ተናገረ( ማር. 10፥32-34 ፤ ሉቃ. 18፥31-34 ) 17 ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ሳለ፥ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወሰዳቸው፥ በመንገድም ሳሉ እንዲህ አላቸው፦ 18 “እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄድን ነው፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ተላልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ 19 እንዲያላግጡበት፥ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” ስለ ዘብዴዎስ ልጆች( ማር. 10፥35-45 ) 20 በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ከልጆችዋ ጋር ወደ እርሱ ቀረበች። 21 እርሱም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም “እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ እዘዝ” አለችው። 22 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” እነርሱም “እንችላለን” አሉት። 23 እርሱም “ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ መስጠት የእኔ አይደለም ነገር ግን እርሱ በአባቴ ለተዘጋጀላቸው ነው፤” አላቸው። 24 ዐሥሩም ይህንን በሰሙ ጊዜ በሁለቱም ወንድማማቾች ተቆጡ። 25 ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው “የአሕዛብ አለቆች ጌትነታቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታላላቆቹም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታውቃላችሁ። 26 በእናንተ መካከል እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ 27 ከእናንተም መካከል ፊተኛ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባርያ ይሁን፤ 28 የሰው ልጅም ሊያገለግል፥ ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ኢየሱስ ሁለት ዐይነ ስውሮችን መፈወሱ( ማር. 10፥46-52 ፤ ሉቃ. 18፥35-43 ) 29 ከኢያሪኮ ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። 30 እነሆ፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንደሚያልፍ በሰሙ ጊዜ “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ ጮኹ። 31 ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። 32 ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 33 እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው” አሉት። 34 ኢየሱስም አዘነላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ አዩ፥ ተከተሉትም። |