የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


ኢዩኤል 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
ኢዩኤል 2

1 የጌታ ቀን መጥቷልና፥ እርሱም ቀርቧልና በጽዮን መለከትን ንፉ፥ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፥ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ።

2 የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል፥ ከዘለዓለምም ጀምሮ እንደ እነርሱ ያለ አልነበረም፥ ከእነርሱም በኋላ ለብዙ ትውልድ እንደ እነርሱ ያለ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።

3 እሳት በፊታቸው ትባላለች፥ በኋላቸውም ነበልባል ታቃጥላለች፥ ምድሪቱ በፊታቸው እንደ ዔድን ገነት፥ በኋላቸውም የምድረ በዳ በረሃ ናት፥ ከእነርሱም የሚያመልጥ የለም።

4 መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፥ እንደ ፈረሶችም ይሮጣሉ።

5 በተራራ ላይ እንዳሉ ሰረገሎች ድምፅ፥ ገለባውንም እንደሚበላ እንደ እሳት ነበልባል ድምፅ፥ ለሰልፍም እንደ ተዘጋጀ እንደ ብርቱ ሕዝብ ያኰበኩባሉ።

6 ከፊታቸው አሕዛብ ይንቀጠቀጣሉ፥ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቁራል።

7 እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፥ እንደ ጦር ሰዎችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፥ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፥ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም።

8 አንዱ ካንዱ ጋር አይጋፋም፥ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል፥ በጦር መሣርያ መካከል ያልፋሉ፥ የሚያስቆማቸው ነገር የለም።

9 በከተማም ያኰበኩባሉ፥ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፥ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፥ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ።

10 ምድሪቱም ከፊታቸው ትናወጣለች፥ ሰማያትም ይንቀጠቀጣሉ፥ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ።

11 ጌታም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ያሰማል፥ ሠራዊቱ እጅግ ብዙ ነውና፥ ቃሉንም የሚፈጽም እርሱ ኃያል ነውና፥ የጌታ ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል?

12 አሁንስ፥ ይላል ጌታ፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።

13 ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፥ ጌታ አምላካችሁም ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።

14 የሚመለስና የሚጸጸት እንደሆነ፥ ጌታ አምላካችሁም የእህልና የመጠጥ ቁርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደሆነ ማን ያውቃል?

15 በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥

16 ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፥ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ።

17 የጌታም አገልጋዮች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ፦ “አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤” ከአሕዛብ መካከል፦ “አምላካቸው ወዴት ነው?” ስለምን ይበሉ?

18 ጌታም ስለ ምድሩ ቀና፥ ለሕዝቡም ራራለት።

19 ጌታም መልሶ ሕዝቡን፦ እነሆ፥ እህልንና ወይንን ዘይትንም እልክላችኋለሁ፤ እናንተም በእርሱ ትጠግባላችሁ፥ ከእንግዲህም ወዲያ በአሕዛብ መካከል መሰደቢያ አላደርጋችሁም።

20 የሰሜንንም ሠራዊት ከእናንተ ዘንድ አርቃለሁ፥ ወደ በረሃና ወደ ምድረ በዳ፥ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር አድርጌ አሳድደዋለሁ፥ እርሱም ብዙ ነገር አድርጎአልና ግማቱ ይወጣል፥ ክርፋቱም ይነሣል አለ።

21 ምድር ሆይ፥ ጌታ ታላቅ ነገር አድርጎአልና አትፍሪ፥ ደስም ይበልሽ፥ እልልም በዪ።

22 እናንተ የምድር እንስሶች ሆይ፥ የምድረ በዳው ማሰማርያ ለምልሞአልና፥ ዛፉም ፍሬውን አፍርቶአልና፥ በለሱና ወይኑም ኃይላቸውን ሰጥተዋልና አትፍሩ።

23 እናንተ የጽዮን ልጆች፥ ጌታ አምላካችሁ ቀድሞ የሚደርሰውን ዝናብ ስለ ጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፥ እንደ በፊትም ቀዳሚውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ፥ ለእርሱም እልል በሉ።

24 አውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፥ መጥመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ።

25 የሰደድሁባችሁ ታላቁ ሠራዊቴ አንበጣና ደጎብያ ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ።

26 ብዙ መብል ትበላላችሁ፥ ትጠግቡማላችሁ፥ ከእናንተም ጋር ተአምራትን የሠራውን የጌታ የአምላካችሁን ስም ታመሰግናላችሁ፥ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም።

27 እኔም በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፥ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ፥ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፥ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም።

28 ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፥ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ወጣቶቻችሁም ራእይ ያያሉ፥

29 ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎች ላይም መንፈሴን አፈስሳለሁ፥

30 በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፥ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ ይሆናል።

31 ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።

32 እንዲህም ይሆናል፥ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፥ ጌታም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም የሚተርፉ ይኖራሉ። ደግሞም ጌታ የጠራቸው ይገኛሉ።