የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


1 ሳሙኤል 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
1 ሳሙኤል 2

የሐና ዝማሬ

1 ሐናም እንዲህ ብላ ጸለየች፦ “ልቤ በጌታ ደስ ይለዋል፥ ቀንዴም በጌታ ከፍ ከፍ ብሏል፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛልና፥ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ።

2 እንደ ጌታ ያለ ቅዱስ የለም፥ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችንን የሚመስልም ዓለት የለም።

3 እጅግ በመኩራራት አትናገሩ፥ የእብሪትም ቃል ከአፋችሁ አይውጣ፥ ጌታ አምላክ አዋቂ ነውና፥ በእርሱም ሥራዎች ይመዘናሉ።

4 የኀያላን ቀስቶች ተሰበሩ፤ ደካሞች ግን በብርታት ታጥቀዋል።

5 ጠግበው የነበሩ አጥተው ለእንጀራ ተገዙ፤ ተርበው የነበሩ ግን ከራብ ዐርፈዋል። መካኒቱ ሰባት ወለደች፥ ብዙ የወለደችው ግን ብቻዋን ቀረች።

6 ጌታ ይገድላል፤ ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ከሲኦልም ያወጣል።

7 ጌታ ድሀ ያደርጋል፤ ሀብታምም ያደርጋል፤ ያዋርዳል ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል።

8 ወደ ልዑላንም ደረጃ ከፍ ሊያደርጋቸው፥ የክብርንም ዙፋን ሊያወርሳቸው፥ እርሱ ድኾችን ከትቢያ፥ ምስኪኖችንም ከዐመድ ላይ ያነሣል፤ የምድር መሠረቶች የጌታ ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አኖረ።

9 እርሱ የታማኞቹን እግር ይጠብቃል ሰው በኃይሉ አይበረታምና፥ ኃጥአን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይጣላሉ።

10 ጌታ! እርሱን የሚቃወሙ ይደቅቃሉ፥ ከሰማይም ያንጐደጉድባቸዋል፥ ጌታ እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፥ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፥ የመሢሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”

የዔሊ ልጆች ክፉ ሥራ

11 ሕልቃናም ወደ ቤቱ ወደ ራማ ሄደ፤ ብላቴናውም በካህኑ በዔሊ ፊት ጌታን ያገለግል ነበር።

12 የዔሊም ልጆች ለጌታ ክብር የማይሰጡ ስድ አደጎች ነበሩ።

13 የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፥ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ አገልጋይ ይመጣ ነበረ፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፥

14 ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ይህንንም ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ ያደርጉ ነበር።

15 ከዚህም ሌላ፥ ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ አገልጋይ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፦ “ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር።

16 ሰውየውም፦ “አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት፥ ከዚያም በኋላ ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ያህል ትወስዳለህ” ቢለው፥ እርሱ፦ “አይሆንም፥ አሁን ልትሰጠኝ ይገባል፤ ካልሆነ ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር።

17 በዚህም ዓይነት የጌታን መሥዋዕት ስላቃለሉ፥ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በጌታ ፊት ከፍተኛ ነበር።

ሳሙኤል በሴሎ

18 ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በጌታ ፊት ያገለግል ነበር።

19 እናቱም በየዓመቱ ከባሏ ጋር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር።

20 ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን፦ “ለጌታ ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት ጌታ ዘር ይስጥህ” ብሎ ባረካቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር።

21 ጌታም ሐናን አሰበ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በጌታ ፊት አደገ።

ዔሊና ልጆቹ

22 ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ።

23 እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና፥ ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?

24 ልጆቼ ሆይ፥ የጌታን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም።

25 ሰውስ በሰው ቢበድል እግዚአብሔር ይታደገዋል፤ ሰው ግን ጌታን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው?” እነርሱ ግን ጌታ ሊገድላቸው ወድዷልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም።

26 ብላቴናው ሳሙኤልም እያደገና፥ በጌታም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ።

በዔሊ ቤተሰብ ላይ የተነገረ ትንቢት

27 አንድ እግዚአብሔር ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘በግብጽ በፈርዖን ቤት ባርያ ሳሉ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፤

28 ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬ ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ኤፋድንም በፊቴ እንዲለብስ ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የሚያቀርቡትን የሚቃጠል መሥዋዕት ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።

29 በማደሪያዬ እንዲያቀርቡት ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቁርባኔን ስለምን ረገጣችሁ? ሕዝቤ እስራኤል ካቀረበው ቁርባን ሁሉ ምርጥ ምርጡን በልታችሁ ራሳችሁን በማወፈር፥ ከእኔ ይልቅ ለልጆችህ ስለምን ክብር ሰጠህ?’

30 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በእውነት ቤትህ፥ የአባትህም ቤት ለዘለዓለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤’ አሁን ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ ከእኔ ይራቅ።

31 እነሆ፥ ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ፥ የአንተንም ክንድ፥ የአባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል።

32 እነሆ በእስራኤል በረከት ሁሉ በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ፤ በቤትህም ለዘለዓለም ሽማግሌ አይገኝም።

33 በመሠዊያዬ ከምታገለግሉት ከእናንተ መካከል ሳላጠፋ የማስቀረው አንድ ሰው ዐይንህን በእንባ የሚያጠፋና ልብህን የሚያሳዝን ይሆናል፤ የቤተሰብህ አባሎች ሁሉ ግን በሰዎች ሰይፍ ያልቃሉ።

34 ይህ በሁለቱ ልጆችህ በሖፍኒና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፤ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ።

35 የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፤ እንደ ልቤና እንደ ሐሳቤም የሚያደርግ ይሆናል፤ እኔም የጸና ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑንም ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል።

36 ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፤ በፊቱም ሰግዶ፦ ቁራሽ እንጀራ እንድበላ ከካህናት ስፍራ ወደ አንዲቱ፥ እባክህ፥ ስደደኝ ብሎ የዕለት ምግብ ብቻ ለማግኘት ይለምናል።’”