ዕንባቆም 1:6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ለመውረስ በምድር ሁሉ ላይ የሚሄዱትን፥ መራሮችና ችኩሎች ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የራሳቸው ያልሆኑትን መኖሪያ ስፍራዎች ለመያዝ፣ ምድርን ሁሉ የሚወርሩትን፣ ጨካኝና ፈጣን የሆኑትን፣ ባቢሎናውያንን አስነሣለሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነሆ እነዚያን ጨካኞችና ችኲሎች ባቢሎናውያንን አስነሣባችኋለሁ፤ እነርሱ የራሳቸው ያልሆነውን ምድር ሁሉ በጦር ኀይል ለመያዝ በየሀገሩ ይዞራሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። |
እግዚአብሔር ባገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት ይሁዳን ስለ ማጥፋት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ወራሪ ቡድኖች ባቢሎናውያንን፥ ሶርያውያንን፥ ሞአባውያንንና ዐሞናውያንን በኢዮአቄም ላይ አስነሣበት።
ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጉልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጎልማሳውንና ድንግሊቱን ሽማግሌውንና አዛውንቱን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።
እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት።
‘የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥ በቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን የጦር መሣርያ እመልሳለሁ፥ እነርሱንም ወደዚህች ከተማ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ።
ከዚህ በኋላ፥ ይላል ጌታ፥ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን፥ ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህችም ከተማ የቀሩትን፥ አገልጋዮቹንና ሕዝቡን በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፥ አይራራላቸውም፥ አይምራቸውም።’
እነሆ፥ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ እልካለሁ ይላል ጌታ፥ ባርያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች፥ በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመሣቀቂያና ለማፍዋጫም ለዘለዓለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ።
በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም፦ “ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከተራቈቱ ኮረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ ይመጣል፤
የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ፥ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ጽኑ ጥንታዊ ሕዝብ ነው፥ ቋንቋቸውንም የማታውቀው የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው።
ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉም በግፍ ለሚገኝ ጥቅም ስስታም ነውና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉም በተንኰል ያደርጋሉና ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ።
ባዕዳን፥ የሕዝቦች ጨካኞች የሆኑ፥ ቆርጠው ጣሉት፤ በተራሮች እና በሸለቆዎች ሁሉ ውስጥ ቅርጫፎቹ ወደቁ፥ ቅርንጫፎቹም በምድር ፈሳሾች ሁሉ ላይ ተሰባበሩ፥ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ ከጥላው ወጥተው ትተውት ሄዱ።
እሳት በፊታቸው ትባላለች፥ በኋላቸውም ነበልባል ታቃጥላለች፥ ምድሪቱ በፊታቸው እንደ ዔድን ገነት፥ በኋላቸውም የምድረ በዳ በረሃ ናት፥ ከእነርሱም የሚያመልጥ የለም።