Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ነገሥት 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ኢዮአቄም በነገሠ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይሁዳን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ከገበረለት በኋላ እንደገና ዐመፀ፤

2 እግዚአብሔር ባገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት ይሁዳን ስለ ማጥፋት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ወራሪ ቡድኖች ባቢሎናውያንን፥ ሶርያውያንን፥ ሞአባውያንንና ዐሞናውያንን በኢዮአቄም ላይ አስነሣበት።

3 ይህም ሁሉ የሆነው ንጉሥ ምናሴ ስለ ፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የይሁዳን ሕዝብ ከፊቱ ለማስወገድ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ነው፤

4 በተለይም ምናሴ የንጹሓን ሰዎችን ደም በማፍሰሱና ኢየሩሳሌምንም በንጹሓን ደም በመሙላቱ ምክንያት ይህ ሁሉ ሊፈጸም ችሎአል፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለምናሴ ምሕረት ሊያደርግለት አልፈቀደም።

5 ኢዮአቄም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤

6 ኢዮአቄም ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢኮንያን ነገሠ።

7 የባቢሎን ንጉሥ ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ግብጽ ሰሜናዊ ጠረፍ ድረስ የግብጽ ይዞታ የነበረውን ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ስለ ነበረ የግብጽ ንጉሥና ሠራዊቱ ከዚያን በኋላ ከግብጽ ውጪ ዘመቻ አላደረጉም፤


የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን
( 2ዜ.መ. 36፥9-10 )

8 ኢኮንያን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም ነሑሽታ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ የሆነው የኤልናታን ልጅ ነበረች።

9 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

10 በናቡከደነፆር የጦር አዛዦች የሚመራው የባቢሎን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ዘምቶ የከበባትም በዚሁ በዮአኪን ዘመነ መንግሥት ነበር።

11 በከበባውም ጊዜ ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤

12 ንጉሥ ኢኮንያን ከእናቱ፥ ከልዑላን መሳፍንቱ፥ ከጦር አዛዦቹና ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለ ሥልጣኖች ጋር ቀርቦ ለባቢሎናውያን እጁን ሰጠ፤ ናቡከደነፆር በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ኢኮንያንን እስረኛ አድርጎ ያዘው፤

13 በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ ጠራርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደ። ቀደም ሲል እግዚአብሔር በተናገረውም ቃል መሠረት ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አሠርቶት የነበረውን የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰባበረው።

14 ናቡከደነፆር የኢየሩሳሌምን ሕዝብ፥ ልዑላን መሳፍንቱን ሁሉና ሌሎችንም ታላላቅ ሰዎችን ጭምር በድምሩ ዐሥር ሺህ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፤ ከእነርሱም ጋር የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎችንና የብረት አንጣሪዎችን ሁሉ ወሰደ፤ በይሁዳ እንዲቀሩ ያደረገው የመጨረሻዎችን ድኾች ብቻ ነበር።

15 ናቡከደነፆር ኢኮንያንን አስሮ ከነእናቱ ከሚስቶቹ፥ ባለሟሎቹ ከሆኑ ባለሥልጣኖችና ከይሁዳ ታላላቅ ሰዎች ጋር በአንድነት ሰብስቦ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።

16 የባቢሎን ንጉሥ ሰባት ሺህ ለውጊያ ብቃት ያላቸው ወንዶችን፥ እንዲሁም አንድ ሺህ ብረት ቀጥቃጮችንና እደ ጥበበኞችን ወደ ባቢሎን ወሰደ።

17 ናቡከደነፆር በኢኮንያን ምትክ ማታንያ ተብሎ የሚጠራውን የዮአኪንን አጐት በይሁዳ አነገሠ፤ ስሙንም በመለወጥ ሴዴቅያስ ብሎ ጠራው።


የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ
( 2ዜ.መ. 36፥11-12 ፤ ኤር. 52፥1-3 )

18 ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሀያ አንድ ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሐሙጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የነበረው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፤

19 ኢዮአቄም ባደረገው ዓይነት ሴዴቅያስ ክፉ አደረገ።

20 እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሕዝብ ላይ ተቆጥቶ ከፊቱ አስወገዳቸው፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች