ኤርምያስ 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የባቢሎን ምርኮ አስቀድሞ መነገሩ 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በመጀመሪያው ዓመት፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 ይህንም ቃል ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 3 ከይሁዳ ንጉሥ ከአሞጽ ልጅ ከኢዮስያስ ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባሉት በእነዚህ በሀያ ሦስቱ ዓመታት፥ የጌታ ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እኔም ማልጄ ተነሥቼ ተናገርኋችሁ፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም ግን አልሰማችሁም። 4 ጌታም ማልዶ ተነሥቶ ባርያዎቹን ነቢያትን ሁሉ ወደ እናንተ ላከ፤ ልኮም ግን እናንተ አላደመጣችሁም፥ ለመስማትም ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም። 5 እርሱም፦ ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤ ጌታም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ምድር ተቀመጡ። 6 ልታገለግሉአቸውና ልትሰግዱላቸው ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ክፉም እንዳላደርግባችሁ በእጃችሁ ሥራ አታስቈጡኝ አለ። 7 ለእናንተ ጉዳት እንዲሆን በእጃችሁ ሥራ አስቆጣችሁኝ እንጂ አልሰማችሁኝም፥ ይላል ጌታ። 8 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቃሎቼን አልሰማችሁምና 9 እነሆ፥ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ እልካለሁ ይላል ጌታ፥ ባርያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች፥ በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመሣቀቂያና ለማፍዋጫም ለዘለዓለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። 10 ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራይቱን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። 11 ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ትሆናለች፤ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ያገለግላሉ። 12 ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ሕዝብ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል ጌታ፥ የከለዳውያንንም ምድር ለዘለዓለም ባድማ አደርጋታለሁ። 13 በእርሷም ላይ የተናገርሁትን ቃሎቼን ሁሉ፥ ማለት ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ትንቢት የተናገረውን በዚህች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር አመጣለሁ። 14 ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት ደግሞ እነርሱን ይገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ። የጌታ የቁጣው ጽዋ 15 የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ አለኝ፦ “የዚህን ቁጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ አንተንም የምልክባቸውን አሕዛብን ሁሉ አጠጣቸው። 16 በመካከላቸውም ከምልከው ሰይፍ የተነሣ ይጠጣሉ ይወላገዳሉም ያብዳሉም።” 17 ከጌታም እጅ ጽዋውን ወሰድሁ፥ ጌታም እኔን የላከባቸውን አሕዛብ ሁሉ አጠጣኋቸው። 18 ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ማፍዋጫም እርግማንም ላደርጋቸው፥ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ነገሥታትዋንም አለቆችዋንም አጠጣኋቸው። 19 የግብጽንም ንጉሥ ፈርዖንን ባርያዎቹንም አለቆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ፥ 20 የተደባለቀውንም ሕዝብ ሁሉ፥ የዑፅ ምድር ነገሥታትንም ሁሉ፥ የፍልስጥኤም ምድር ነገሥታትንም ሁሉ አስቀሎናንም ጋዛንም አቃሮንንም የአዛጦንንም ትሩፍ፥ 21 ኤዶምያስንም፥ ሞአብንም፥ የአሞንም ልጆች፥ 22 የጤሮስን ነገሥታትም ሁሉ፥ የሲዶናን ነገሥታትም ሁሉ፥ በባሕር ማዶ ያለች የደሴት ነገሥታትንም፥ 23 ድዳንንም፥ ቴማንንም፥ ቡዝንም፥ የጠጉራቸውንም ማዕዘን የሚቈርጡትን ሁሉ፥ 24 የዓረብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድረ በዳ የሚቀመጡ የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ 25 የዘምሪ ነገሥታትንም ሁሉ፥ የኤላም ነገሥታትንም ሁሉ፥ የሜዶን ነገሥታትንም ሁሉ፥ 26 አንዱን ከሌላው በመቀጠል፥ ቅርብና ሩቅ የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድር ፊት ላይ ያሉ የዓለም መንግሥታትንም ሁሉ አጠጣኋቸው፤ የሼሻክም ንጉሥ ከእነርሱ በኋላ ይጠጣል። 27 አንተም፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በመካከላችሁ ከምልከው ሰይፍ የተነሣ ጠጡ፥ ስከሩም፥ አስታውኩም፥ ውደቁም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሡም በላቸው። 28 ጽዋውንም ከእጅህ ተቀብለው ለመጠጣት እንቢ ቢሉ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ፈጽማችሁ ትጠጣላችሁ። 29 እነሆ፥ ስሜ የተጠራባት ከተማ ላይ ክፉን ነገር ማምጣት እጀምራለሁ፤ በውኑ እናንተ ፈጽሞ ያልተቀጣችሁ ትሆናላችሁን? በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ያለ ቅጣት አትቀሩም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ በላቸው። 30 ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ቃላት በእነርሱ ላይ ትንቢት ትናገራለህ፥ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ ጌታ በላይ ሆኖ ይጮኻል፥ በቅዱስ ማደሪያውም ሆኖ ድምፁን ያሰማል፤ በበረቱ ላይ እጅግ ይጮኻል፥ ወይንም እንደሚጠምቁ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይጮኻል። 31 ጌታ ከአሕዛብ ጋር ሙግት አለውና ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፤ ከሥጋ ለባሽ ሁሉ ጋር ይፋረዳል፥ ኃጢአተኞችንም ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል፥ ይላል ጌታ። 32 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፥ ጽኑም ዐውሎ ነፍስ ከምድር ዳርቻዎች ይነሣል። 33 በዚያም ቀን ጌታ የገደላቸው ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ እንጂ አይሰበሰቡም አይቀበሩምም። 34 “ልትታረዱና ልትበተኑ ቀናችሁ ደርሶአልና፥ እንደ ተወደደም የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች፥ አልቅሱ ጩኹም፤ እናንተ የመንጋ አውራዎች፥ በአመድ ውስጥ ተንከባለሉ። 35 ከእረኞችም የመሸሻ ስፍራ ከመንጋ አውራዎችም ማምለጫ ይጠፋል። 36 ጌታ ማሰማርያቸውን አጥፍቶአልና የእረኞች ጩኸት ድምፅ የመንጋ አውራዎችም ልቅሶ ሆኖአል። 37 ከጌታ ጽኑ ቁጣ የተነሣ የሰላም በረት ፈርሶአል። 38 እንደ ደቦል አንበሳ መደቡን ለቅቆአል፤ ከአስጨናቂውም ሰይፍና ከጽኑ ቁጣው የተነሣ ምድራቸው ባድማ ሆናለችና።” |