ገላትያ 3:16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር። ለብዙዎች እንደሆነ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደሆነ “ለዘርህም” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔርም ለአብርሃምና ለዘሩ የተስፋ ቃል የሰጠው በዚህ ዐይነት ነው፤ መጽሐፍ የተስፋ ቃል ከአብርሃም በኋላ የተሰጠው ለብዙዎች እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘርህ” ይላል፤ ይህም “ዘርህ” የተባለው ክርስቶስ ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም ለአብርሃም፥ “ለአንተና ለዘርህ” ብሎ ተስፋ ሰጠው፤ ለብዙዎች እንደሚናገር አድርጎ ለአንተና ለዘሮችህ አላለውም፤ ለአንድ እንደሚናገር አድርጎ፥ “ለዘርህ” አለው እንጂ ይኸውም ክርስቶስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፦ ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፦ ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። |
እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና፦ ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ።
እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ፤’ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ።
ስለዚህ በእምነት የሆነው፥ ተስፋው በእምነት እንዲያርፍና ለዘሩ ሁሉ እንዲሆን ነው፥ ይህም ሕግ ፈፃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የአብርሃምን እምነት የሚጋሩትንም ጭምር ነው፥ እርሱ የሁላችንም አባት ነውና፥
አካልም አንድ እንደሆነ ብዙም የአካል ክፍሎች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ክፍሎች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤
እነርሱ ዕብራውያን ናቸው? እኔም ነኝ፤ የእስራኤል ወገን ናቸው? እኔም ነኝ፤ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም ነኝ፤ የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸው?
መጽሐፍም፥ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፥ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤” ብሎ አስቀድሞ ለአብርሃም ወንጌልን ሰበከለት።
እንዲሁም እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ የሚያድገውን አካል ሁሉ የሚንከባከበውን በመገጣጠምያዎቹና በጅማቶቹ አብሮ የሚያስተሳስረውን ራስ በጽኑ ሳይዝ ማንም አያውግዛችሁ።
በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው።