ገላትያ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)እምነት ወይስ የኦሪትን ሕግ መጠበቅ 1 እናንተ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! ማን መተት አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በዐይኖቻችሁ ላይ ተሥሎ ነበር፤ 2 ከእናንተ ይህን ብቻ መማር እፈልጋለሁ፤ መንፈስን የተቀበላችሁት በሕግ ሥራ ነውን? ወይስ በእምነት በመስማት? 3 እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን ግን በሥጋ ትፈጽማላችሁን? 4 ይህን ሁሉ መከራ የተቀበላችሁት በከንቱ ነውን? እንደዚያ ከሆነ በእርግጥ ከንቱ ነው። 5 እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ድንቅን የሚሠራ፥ በሕግ ሥራ ነውን? ወይስ በእምነት በመስማታችሁ ነው? 6 አብርሃም በእግዚአብሔር እንደ አመነና፥ ጽድቅም ሆኖ እንደ ተቆጠረለት፥ 7 እንግዲህ እነዚህ የሚያምኑት፥ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። 8 መጽሐፍም፥ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፥ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤” ብሎ አስቀድሞ ለአብርሃም ወንጌልን ሰበከለት። 9 ስለዚህም የሚያምኑት ከታመነው ከአብርሃም ጋር ተባርከዋል። 10 ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ የማይኖርና የማይፈጽማቸው ሁሉ የተረገመ ይሁን፤” ተብሎ ተጽፎአልና። 11 “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሏልና፥ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጥ ነው። 12 ሕግ ከእምነት አይደለም፤ ነገር ግን “የሚፈጽማቸው በእነርሱ ይኖራል።” 13 ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ፥ ከሕግ እርግማን ዋጅቶናል፤ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው፤” ተብሎ ተጽፎአልና 14 ይህም የአብርሃም በረከት፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ አሕዛብ እንዲደርስና የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል ነው። የኦሪት ሕግና ተስፋ 15 ወንድሞች ሆይ! እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የጸና ኪዳን፥ የሰው ስንኳ ቢሆን፥ ማንም አያፈርሰውም ወይም አይጨምርበትም። 16 የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር። ለብዙዎች እንደሆነ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደሆነ “ለዘርህም” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። 17 ይህንም እላለሁ፦ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የመጣው ሕግ፥ የተስፋውን ቃል ለማስቀረት፥ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን ሊሽር አይችልም። 18 ውርስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፥ በተስፋ ቃል መሆኑ ይቀር ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ለአብርሃም በተስፋ ቃል አማካይነት ሰጠው። 19 ታዲያ ሕግ ለምንድን ነው? በተስፋ ቃል የተነገረው ዘር እስኪመጣ ድረስ፥ ስለ መተላለፍ ተጨመረ፤ በመላእክት በኩል መካከለኛ እጅ ታዘዘ። 20 መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ስለ ልጆችና አገልጋዮች 21 እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማልን? በጭራሽ አይደለም። ሕይወትን ሊሰጥ የሚችል ሕግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ በእርግጥ ጽድቅ በሕግ በኩል በሆነ ነበር፤ 22 ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ እንዲሰጥ፥ መጽሐፍ ሁሉን ነገር ከኃጢአት በታች ደምድሞታል። 23 እምነት ከመምጣቱ በፊት እምነት እስኪገለጥ ድረስ ተዘግቶብን ከሕግ በታች ሆነን እንጠበቅ ነበር። 24 ስለዚህ በእምነት እንድንጸድቅ፥ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆነ፤ 25 ነገር ግን እምነት ስለ መጣ ከእንግዲህ ወዲህ በሞግዚት ሥር አይደለንም። 26 በክርስቶስ ኢየሱስ ባላችሁ እምነት ሁላችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ 27 ከክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል። 28 በክርስቶስ ኢየሱስ ሁላችሁም አንድ ናችሁና አይሁዳዊ ወይም ግሪካዊ የለም፥ ባርያ ወይም ነጻ ሰው የለም፥ ወንድ ወይም ሴት የለም። 29 የክርስቶስ ከሆናችሁ ስለዚህ የአብርሃም ዘር ናችሁ፥ በተስፋውም ቃል መሠረት ወራሾች ናችሁ። |