Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ተግሣጽ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኃጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተማምኖ ይኖራል። 2 በክፉዎች በደል መቅሠፍት ይነሣል፤ ዐዋቂ ሰው ግን ፈጽሞ ያጠፋዋል። 3 በኀጢአት የጸና ሰው ድሆችን ይቀማል፤ እንደማይጠቅም እንደ ከባድ ዝናብም ነው፥ 4 ሕግን የሚተዉና ኀጢአትን የሚያወድሱ እንደዚሁ ናቸው። ሕግ ጠባቂዎች ግን ለራሳቸው ቅጥርን ይሠራሉ። 5 ክፉዎች ሰዎች ፍርድን አያስተውሉም፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ። 6 ከሐሰተኛ ባለጠጋ፥ በእውነት የሚሄድ ድሃ ይሻላል። 7 ሕግን የሚጠብቅ ልጅ ዐዋቂ ነው፤ አመንዝራ ሴትን የሚመለከት ግን ለጥፋት ይዳረጋል፥ አባቱንም ያሰድባል። 8 በአራጣና በቅሚያ ሀብቱን የሚያበዛ ለድሃ ለሚራራ ያከማችለታል። 9 ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ሰው ጸሎቱ የተናቀ ነው። 10 ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚያስት፥ እርሱ ወደ ጥፋት ይወድቃል፤ ዐመፀኞች ግን በመልካም በኩል ያልፋሉ፥ ወደ ውስጧም አይገቡም። 11 ባለጠጋ ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል፤ አስተዋይ ድሃ ግን ይመረምረዋል። 12 በጻድቃን ረድኤት ብዙ ክብር አለ፤ በኃጥኣን መንገድ ግን ሰዎች ይጠፋሉ። 13 በደሉን የሚሰውር ሰው መንገዱ አይቃናም፤ የሚናዘዝና ራሱን የሚዘልፍ ግን ይወደዳል። 14 ስለ ጽድቅ ሁልጊዜ የሚደነግጥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ይወድቃል። 15 ራሱ ድሃ ሆኖ ሳለ ድሃ ሕዝብን የሚያስጨንቅ ክፉ መኰንን፥ እንደ ተራበ አንበሳና እንደ ተጠማ ተኵላ ነው። 16 አእምሮ የጐደለው ንጉሥ ብዙ ግብርን አስገባሪ ይሆናል፤ ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል። 17 በሰው ደም የሚገባ ዐመፀኛ ሰው ወደ ጕድጓድ በሚገባበት ጊዜ የሚይዘው የለም፥ ለነፍሰ ገዳይም ዋስ የሚሆን ሰው ይሰደዳል፥ በደኅናም አይኖርም። ልጅህን አስተምረው ይወድድሃልም፥ ለነፍስህም ክብርን ይሰጣል። ዐመፀኛ ሕዝብ ሕግን አይሰማም። 18 በጽድቅ መንገድ የሚሄድ ሰው ይረዳል፥ በጠማማ መንገድ የሚሄድ ግን በወጥመድ ይያዛል። 19 ምድሩን የሚያርስ እንጀራን ይጠግባል፤ ሥራ ፈትነትን የሚያበዛ ግን ድህነትን ያበዛል። 20 የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ክፉ ሰው ግን ከቅጣት አይድንም። 21 የጻድቃንን ፊት የማያፍር ሰው ደግ አይደለም፥ እንዲህ ያለ ሰው በቍራሽ እንጀራ ሰውን አሳልፎ ይሰጣል። 22 ምቀኛ ሰው ባለጠጋ ለመሆን ይቸኩላል፥ የሚራራ ሰውም እንደሚገዛው አያውቅም። 23 በምላሱ ከሚሸነግል ሰው ይልቅ የሰውን መንገድ የሚነቅፍ እጅግ ክብርን ያገኛል። 24 ከአባቱና ከእናቱ የሚሰርቅ፥ ኀጢአትንም አልሠራሁም የሚል፥ የአጥፊ ባልንጀራ ነው። 25 የሚሳሳ ሰው ከንቱን ይፈርዳል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በጥንቃቄ ይኖራል። 26 በልቡ ደስታ የሚታመን ሰው እንደዚሁ ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል። 27 ለድሃ የሚሰጥ አይቸገርም፤ ዐይኖቹን የሚያዞር ግን በከባድ ችግር ይኖራል። 28 በኃጥኣን ቦታ ጻድቃን ያለቅሳሉ፥ በእነርሱ ጥፋት ግን ጻድቃን ይበዛሉ። |