ዘሌዋውያን 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለእግዚአብሔር ስለሚቀርበው መባእ የተሰጠ ሕግ 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰውነቱ ዋጋውን ይስጥ። 3 ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ዲድርክም ይሁን። 4 ሴትም ብትሆን ግምቷ ሠላሳ የብር ዲድርክም ይሁን። 5 ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሃያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሃያ የብር ዲድርክም፥ ለሴትም ዐሥር የብር ዲድርክም ይሁን። 6 ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ዲድርክም፥ ለሴትም ግምቷ ሦስት የብር ዲድርክም ይሁን። 7 ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ ዐሥራ አምስት ዲድርክም፥ ለሴትም ዐሥር ዲድርክም ይሁን። 8 ለግምቱ የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፤ ካህኑም የተሳለውን ሰው ከእጁ ባለው ገንዘብ መጠን ይገምትለት፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምትለት። 9 “ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 10 መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ። 11 እንስሳው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያቁመው። 12 መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ካህኑ ይገምተው፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። 13 ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ግን ከግምቱ በላይ አምስተኛ እጅ ይጨምር። 14 “ሰውም ለእግዚአብሔር ቅዱስ ይሆን ዘንድ ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም ክፉ እንደ ሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይቆማል። 15 የተሳለውም ሰው ቤቱን ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ እጅ ይጨምር፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል። 16 “ሰውም ከርስቱ እርሻ ለእግዚአብሔር ቢሳል፥ እንደ መዘራቱ መጠን ይገመት፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ አምሳ ወቄት ብር ይገመታል። 17 እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢሳል፥ እንደ ግምቱ መጠን ይቆማል። 18 እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢሳል፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ገንዘቡን ይቈጥርለታል፤ ከግምቱም ይጐድላል። 19 እርሻውንም የተሳለ ሰው ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ፥ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ እጅ ይጨምር፤ ለእርሱም ይሆናል። 20 እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ እንደ ገና ይቤዠው ዘንድ አይቻለውም። 21 እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ዓመት ሲወጣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ርስቱም ለካህኑ ይሆናል። 22 ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለእግዚአብሔር ቢሳል፥ 23 ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ይቈጥርለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለእግዚአብሔር ይሰጣል። 24 በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደ ነበረው ወደ ሸጠው ሰው ይመለሳል፤ የራሱ ወሰን ምድር ነውና። 25 ግምቱም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሚዛን ይሆናል፤ አንዱ ዲድርክም ሃያ አቦሊ ይሆናል። 26 “ከእንስሳህ የሚወለድ በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው፤ ማንም ይለውጠው ዘንድ አይቻለውም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለእግዚአብሔር ነው። 27 የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምቱ ይቤዠው፤ በእርሱም የዋጋውን አምስተኛ እጅ ይጨምርበታል፤ ባይቤዥም እንደ ግምቱ ይሸጣል። 28 “ለእግዚአብሔርም የተለየ እርም የሆነ ነገር ሁሉ፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፤ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 29 ከሰዎችም መባ ሆኖ የቀረበ ሁሉ እስኪሞት ድረስ አይቤዥም። 30 “የምድርም ዐሥራት፥ ወይም የምድር ዘር፥ ወይም የዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ነው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 31 ሰውም ዐሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ አምስተኛ እጅ ይጨመርበታል። 32 ከበሬም ሁሉ ከዐሥር አንድ፥ ከበግም ሁሉ ከዐሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ ሁሉ ከዐሥር አንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል። 33 መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዠውም።” 34 እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ያስተምራቸው ዘንድ ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው። |