ዘሌዋውያን 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ተቅዋመ ማኅቶት ( ዘፀ. 27፥1-21 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “መብራቱን ሁል ጊዜ እንድታበራበት ለመብራት ጥሩ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 3 በምስክሩ ድንኳን ከመጋረጃው ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁል ጊዜ ያበሩታል፤ ለዘለዓለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዐት ይሁን። 4 በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁል ጊዜ እስኪነጋ አብሩአቸው። ስለ ኅብስተ ገጽ 5 “የስንዴ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በእያንዳንዱ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ይሁን። 6 እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ገበታ ላይ አኑራቸው። 7 በሁለቱም ተራ ንጹሕ ዕጣንና ጨው ታደርጋለህ፤ እነዚህም ነገሮች በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ ለተዘጋጁት ኅብስቶች ይሁኑ። 8 በእግዚአብሔር ፊት ሁል ጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ ያድርጉት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ነው። 9 ለአሮንና ለልጆቹም ይሁን፤ በእሳት ከተደረገው ከእግዚአብሔር ቍርባን ለዘለዓለም ሥርዐት ለእርሱ ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት።” በእግዚአብሔር ላይ ስለሚደረግ ፅርፈት ቅጣት 10 አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ሴት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ሴት ልጅና አንድ እስራኤላዊ ሰው በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤ 11 የእስራኤላዊቱም ሴት ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ሰደበ፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የዳቤር ልጅ ነበረች፤ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። 12 በእግዚአብሔርም ትእዛዝ እስኪፈርዱበት ድረስ በግዞት አኖሩት። 13 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 14 “ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት።” 15 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራለህ፥ “ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኀጢአቱን ይሸከማል። 16 የእግዚአብሔርንም ስም ጠርቶ የሚሰድብ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የሀገር ልጅ ቢሆን፥ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ቢሳደብ ይገደል። 17 ሰውን የገደለ ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። 18 እንስሳንም ቢገድል በነፍስ ፋንታ ነፍስ ይክፈል። 19 ሰውም ባልንጀራውን ቢጎዳ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። 20 ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዐይን በዐይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጎዳ እንዲሁ ይደረግበት። 21 ሰውንም የመታና የገደለ ፈጽሞ ይገደል። 22 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለሀገር ልጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይሁንላችሁ።” 23 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈር ወደ ውጭ አወጡት፤ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። |