ዘሌዋውያን 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ደም መብላት ስለ መከልከሉ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው- 2 “ለአሮንና ለልጆቹ፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገር፦ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ እንዲህም አለ፦ 3 ከእስራኤል ቤት ከመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው በሬ፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ቢያርድ፥ በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥ 4 ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው የተመረጠ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ወይም የድኅነት መሥዋዕት ያደርገው ዘንድ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ በሌላም ቦታ ቢያርደው፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር ቍርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ ምስክሩ ድንኳን ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአልና፤ ያም ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 5 ስለዚህ የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ወደ ካህኑም አምጥተው ለእግዚአብሔር ለድኅነት መሥዋዕት ይሠዉታል። 6 ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደሙን ይረጨዋል፤ ስቡንም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን ያቃጥለዋል። 7 መሥዋዕታቸውንም ደግሞ ተከትለው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት አይሠዉ። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ሥርዐት ይሁን።” 8 ለእነርሱ እንዲህ በላቸው፥ “ከእስራኤል ቤት ከመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ 9 ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 10 “ከእስራኤልም ልጆች፥ ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፤ ያንም ሰው ከሕዝቡ ለይች አጠፋዋለሁ። 11 የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነው፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። 12 ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች፦ ‘ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፤ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም’ አልሁ። 13 “ከእስራኤልም ልጆች፥ ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ እያደነ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል፤ በአፈርም ይከድነዋል። 14 የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና፤ ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች፦ የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ አልኋቸው። 15 የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የሀገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፤ በውኃም ይታጠባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 16 ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኀጢአቱን ይሸከማል።” |