ዘሌዋውያን 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሴት ከወለደች በኋላ ከሕርስ ስለምትነጻበት ጊዜ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ ሴት ብታረግዝ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያህል የረከሰች ናት፤ 3 እንደ ግዳጅዋ ወራት ትረክሳለች። በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ። 4 ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቈይ፤ የመንጻቷ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ፤ ወደ መቅደስም አትግባ። 5 ሴት ልጅም ብትወልድ እንደ ግዳጅዋ ወራት ሁለት ሳምንት ያህል የረከሰች ናት፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስድሳ ስድስት ቀን ትቈይ። 6 “የመንጻቷ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ለኀጢአት መሥዋዕት ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታመጣለች። 7 ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ ያስተሰርይላትማል፤ ከደምዋም ፈሳሽ ትነጻለች። ወንድ ወይም ሴት ለምትወልድ ሴት ሕጉ ይህ ነው። 8 ጠቦት ለማምጣት የሚበቃ ገንዘብ በእጅዋ ባይኖራት ሁለት ዋኖሶች፥ ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባለች፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፤ እርስዋም ትነጻለች።” |