ኢሳይያስ 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ኢየሩሳሌም የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ጽዮን ሸለቆ የተነገረ ቃል። እናንተ ሁላችሁ፥ ዛሬ ወደ ሰገነት በከንቱ መውጣታችሁ ምን ሆናችኋል? 2 ጩኸትና ፍጅትም የተሞላብሽ ከተማ ሆይ፥ ቍስለኞችሽ በሰይፍ የቈሰሉ አይደሉም፤ በአንቺ ውስጥ የተገደሉትም በሰልፍ የተገደሉ አይደሉም። 3 ነገር ግን አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፤ የተማረኩትንም በእግር ብረት አሠቃዩአቸው፤ ኀይለኞችሽም ርቀው ሸሹ። 4 ስለዚህ፥ “ተዉኝ እኔ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋትም ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ፥” አልሁ። 5 ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሁከትና የጥፋት፥ የመረገጥና የስብራትም ቀን በጽዮን ሸለቆ ውስጥ ሆኖአል። ታናሹና ታላቁም ሸሽተው በተራራ ላይ ይቅበዘበዛሉ። 6 የኤላምም ሰዎች አፎታቸውን ተሸከሙ፤ በፈረስ የተቀመጡና አርበኞች ሰዎች፥ የአርበኞችም ሠራዊት ነበሩ። 7 መልካሞቹን ሸለቆችሽንም ሰረገሎች ሞሉባቸው፤ ፈረሰኞችም መቆሚያቸውን በበሮችሽ ላይ አደረጉ። 8 የይሁዳንም በሮች ይከፍታሉ፤ በዚያም ቀን የከተማይቱን መኳንንት ቤቶች ይበረብራሉ። የዳዊት ቤት መዛግብትንም ይከፍታሉ። 9 የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደበዙ አይታችኋል፤ የታችኛውንም ኵሬ ውኃ በከተማ አከማችታችኋል፤ 10 የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩንም ለማጽናት ቤቶችን አፈረሳችሁ። 11 በአሮጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፤ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፤ ቀድሞ የሠራውንም አላያችሁም። 12 በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ልቅሶንና ዋይታን፥ ራስን መንጨትንና ማቅን መልበስን ጠራ። 13 እነሆም፥ በዓልን፥ ደስታንና ሐሴትን አደረጋችሁ፤ በሬዎችንና በጎችንም አረዳችሁ፤ “ነገ እንሞታለን፤ እንብላ፤ እንጠጣም፤” እያላችሁ ሥጋን በላችሁ፤ ወይንንም ጠጣችሁ። 14 ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ፥ “እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 15 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፥ “ወደ ገንዘብ ጠባቂው ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው፦ 16 መቃብር በዚያ ያስወቀርህ፥ ከፍ ባለው ስፍራ መቃብር ያሠራህ፥ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖርያ ያሳነጽህ ወደዚህ ለምን መጣህ? ለምንስ በዚህ ተደፋፈርህ? 17 እነሆ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በኀይል ወርውሮ ይጥልሃል፤ ያጠፋሃልም፤ ልብስህንና የክብር አክሊልህንም ይገፍሃል፤ 18 ወደ መከራ ሀገር ይጥልሃል፤ በዚያም ትሞታለህ፤ ያማረ ሰረገላህንም ያጐሰቍለዋል፤ የአለቃህም ቤት ይረገጣል። 19 ከአዛዥነት ሥራህና ከሥልጣንህ ትሻራለህ። 20 በዚያም ቀን ባሪያዬን የኬልቅዩን ልጅ ኤልያቄምን እጠራዋለሁ፤ 21 መጐናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፤ አክሊልህንም እሰጠዋለሁ፤ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩና በይሁዳም ለሚኖሩ አባት ይሆናል። 22 የዳዊትንም ክብር እሰጠዋለሁ፤ ይገዛል፤ በአገዛዝም የሚበልጠው የለም። የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል፤ የሚዘጋም የለም፤ እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም። 23 በታመነ ስፍራ እንደ ችንካር እተክለዋለሁ፤ በአባቱም ቤት የክብር ዙፋን አስቀምጠዋለሁ። 24 የአባቱንም ቤት ክብር ሁሉ፥ ልጆቹንም፥ የልጅ ልጆቹንም፥ ከጽዋ ዕቃ ጀምሮ እስከ ማድጋ ዕቃ ድረስ፥ ታናናሹንና ታላላቁን ሁሉ ይሰቅሉበታል። 25 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በታመነው ስፍራ የተተከለው ችንካር ይወልቃል፤ ተሰብሮም ይወድቃል፤ በእርሱም ላይ የተሰቀለው ሸክም ይጠፋል፤” እግዚአብሔር እንዲህ ተናግሮአልና። |