ዕብራውያን 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ሰንበት 1 እንግዲህ አንፍራ፤ ወደ ዕረፍቱም እንድንገባ ትእዛዙን አንተው፤ ከእናንተም ምንአልባት በተለመደ ስሕተት የሚገኝና የሚጸና ቢኖር ወደ ዕረፍቱ እንዲገባ የሚተዉት አይምሰለው። 2 ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛም የምሥራች ተሰብኮልናል፤ ነገር ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። 3 ሥራዉ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፥ “እንግዲህ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቍጣዬ ማልሁ” እንዳለ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። 4 ስለ ሰባተኛውም ቀን፥ “እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሎአልና። 5 ዳግመኛም፥ “ወደ ዕረፍቴ አይገቡም” ብሎአል። 6 እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ መንገድ ስለ ነበራቸው ቀድሞም የምሥራች የተሰበከላቸው ባለ መታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፦ 7 “ዛሬ ቃሉን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤” በፊት እንደ ተባለ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፥ “ዛሬ” ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። 8 ኢያሱ አሳርፎአቸው ቢሆን ኖሮስ፥ ከብዙ ዘመን በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረም ነበር። 9 እንኪያስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚገቡበት ጸንቶ የሚኖር ዕረፍት እንዳለ ታወቀ። 10 ወደ ዕረፍቱ የገባስ እግዚአብሔር ከሥራው እንደ ዐረፈ፥ እነሆ፥ እርሱ ከሥራው ሁሉ ዐረፈ። 11 እንግዲህ እንደ እነዚያ እንደ ካዱት እንዳንወድቅ፥ ወደ ዕረፍቱ እንገባ ዘንድ እንፋጠን። 12 የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍም ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም፥ ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል። 13 እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዐይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። ስለ ሰማያዊው ሊቀ ካህናት 14 እንግዲህ ወደ ሰማያት የወጣ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፤ በእርሱ በማመን ጸንተን እንኑር። 15 ሊቀ ካህናታችን ለድካማችን መከራ መቀበልን የማይችል አይደለምና፤ ነገር ግን ከብቻዋ ከኀጢአት በቀር እኛን በመሰለበት ሁሉ የተፈተነ ነው። 16 እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል፥ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፥ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። |