ዕዝራ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አይሁድ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው 1 በኤርምያስ አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ከተፈጸመ በኋላ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፤ ደግሞም በጽሕፈት እንዲህ አለ፦ 2 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤትን እሠራለት ዘንድ እንዳስብ አደረገኝ፤ 3 ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤትን ይሥራ፤ 4 በስደት በሚኖርባቸው ከተሞች ሁሉ ለቀረው ሰው ሁሉ የሀገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ፥ በዕቃም፥ በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን።” 5 የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆችም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ። 6 በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና በወርቅ፥ በገንዘቦችና በእንስሶች፥ በሌላም ስጦታ ይረዷቸው ነበር። 7 ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአምላኩ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች አወጣ። 8 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም የመዝገብ ሐላፊ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፤ ለይሁዳም መስፍን ለሲሳብሳር ቈጠራቸው። 9 ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ ሳሕኖች፥ አንድ ሺህም የብር ሳሕኖች፥ ሃያ ዘጠኝም ቢላዋዎች፥ ሠላሳ የወርቅ ዳካዎች፥ 10 አራት መቶ ዐሥርም ሌላ ዓይነት የብር ዳካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ። 11 የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሲሳብሳር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞች ጋር ወሰደ። |