ዘፀአት 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ መጨረሻው መቅሠፍት ማስጠንቀቂያ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ ገና አንዲት መቅሠፍት አመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ ከዚያ ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም ከመነሻ ገንዘብ ጋር ይሰድዳችኋል። 2 ወንዱ ከወዳጁ፥ ሴቲቱም ከወዳጅዋ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስም ይዋሱ ዘንድ በሕዝቡ ጆሮ በስውር ተናገር።” 3 እግዚአብሔርም በግብፃውያን ፊት ለሕዝቡ ሞገስን ሰጠ፤ አዋሱአቸውም፤ ይህ ሙሴም በግብፃውያንና በፈርዖን፥ በሹሞቹም ፊት እጅግ የከበረ ሰው ነበረ። 4 ሙሴም አለ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእኩለ ሌሊት እኔ በግብፅ መካከል እገባለሁ፤ 5 በግብፅም ሀገር ያለ በኵር ሁሉ፥ በዙፋኑ ከሚቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በወፍጮ እግር እስካለችው እስከ አገልጋዪቱ በኵር ድረስ፥ የከብቱም በኵር ሁሉ ይሞታል። 6 በግብፅም ሀገር ሁሉ አስቀድሞ እንደ እርሱ ያልሆነ፥ ኋላም ደግሞ እንደ እርሱ የማይሆን ታላቅ ጩኸት ይሆናል። 7 እግዚአብሔር ግን በግብፃውያንና በእስራኤል መካከል ታላቅ ልዩነትን እንደሚያደርግ እንድታውቁ በእስራኤል ልጆች መካከል ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ውሻ ምላሱን አያንቀሳቅስባቸውም። 8 እነዚህ አገልጋዮችህ ሁሉ፦ አንተ ውጣ፤ የሚከተሉህም ሕዝብ ሁሉ ከዚያች ምድር ይውጡ እያሉ ወደ እኔ ይወርዳሉ፤ ለእኔም ይሰግዳሉ፤ ከዚያም በኋላ እወጣለሁ።” ሙሴም በጽኑ ቍጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ተአምራቴና ድንቄ በግብፅ ሀገር ብዙ እንዲሆን ፈርዖን አይሰማችሁም።” 10 ሙሴና አሮንም እነዚህን ተአምራቶችና ድንቆች ሁሉ በፈርዖን ፊት አደረጉ፤ እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ ምድር ለመልቀቅ እንቢ አለ። |