Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ሄኖክ 41 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከብዙ ቀንም በኋላ ልጄ ማቱሳላ ለልጁ ላሜህ ሚስት አጋባው፤ ከእርሱም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች። 2 ሰውነቱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፥ እንደ ጽጌረዳም ቀይ ነው፤ የራሱም ጠጕር እንደ ባዘቶ ነጭ ነው፤ የተሸራሸም ነው፤ ዐይኖቹም ያማሩ ናቸው። 3 ዐይኖቹንም በገለጠ ጊዜ ቤቱን ሁሉ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ቤቱም ሁሉ ፈጽሞ በራ፤ ከአዋላጂቱም እጅ በተነሣ ጊዜ አፉን ከፈተ፤ የጽድቅ ጌታንም ክብር ተናገረ። 4 አባቱ ላሜህም ከእርሱ የተነሣ ፈርቶ ሸሸ፥ ወደ አባቱም ወደ ማቱሳላ መጣ፤ እንዲህም አለ- “እኔ ልውጥ ልጅ ወለድሁ፤ እንደ ሰውም አይደለም። 5 የሰማይ መላእክት ልጆችንም ይመስላል፤ ፍጥረቱም ልዩ ናት፤ እንደ እኛም አይደለም፤ ዐይኖቹም እንደ ፀሐይ ጨረር ናቸው፤ ፊቱም የበራ ነው። 6 ከመላእክት ነው እንጂ ከእኔ ያልተወለደ ይመስለኛል፥ እኔስ በምድር ላይ በዘመኑ ድንቅ ሥራ እንዳይሠራ ብዬ እፈራለሁ። 7 “አሁንም አባቴ ወደ አባታችን ወደ ሄኖክ ትሄድና እውነቱን ከእርሱ ትሰማ ዘንድ እማልድሃለሁ፤ እለምንሃለሁም። መኖሪያው ከመላእክት ጋር ነውና።” 8 ማቱሳላም የልጁን ነገር በሰማ ጊዜ እኔ በዚያ እንደ አለሁ ሰምትWaልና ወደ ምድር ዳርቻ ወደ እኔ መጣ። 9 ጮኸ፤ እኔም ቃሉን ሰማሁት። ወደ እርሱም መጣሁ፤ “ወደ እኔ መጥተሃልና ልጄ፥ እነሆ፥ አለሁ” አልሁት። 10 እርሱም መለሰልኝ፥ እንዲህም አለኝ- “ስለ ታላቁ ነገርና ስለ ቀረብሁበት አስጨናቂ ራእይ ወደ አንተ መጣሁ። 11 አሁንም አባቴ ሆይ! ስማኝ፤ መልኩና ፍጥረቱ እንደ ሰው ፍጥረት ያልሆነ፥ መልኩም ከበረዶ ይልቅ የሚነጣ፥ ከጽጌረዳም የሚቀላ፥ የራሱም ጠጕር ከነጭ ባዘቶ ይልቅ የሚነጣ፥ ዐይኖቹም እንደ ፀሐይ ጨረር የሚያበሩ ልጅ ለልጄ ለላሜህ ተወልዷልና። 12 ዐይኖቹንም በገለጠ ጊዜ ቤቱን ሁሉ አበራ፤ ከአዋላጂቱም እጅ ተነሣ፤ አፉንም ፈትቶ የሰማይን ጌታ አመሰገነው። 13 አባቱ ልጄ ላሜህም ፈርቶ ወደ እኔ ሸሸ፤ ከሰማይ መላእክት የተወለደ አስመሰለው እንጂ ከእርሱ እንደ ተወለደ አላመነም። 14 እነሆም፥ እውነቱን ትነግረኝ ዘንድ እኔ ወደ አንተ መጣሁ።” 15 እኔም ሄኖክ ስለ እርሱ መለስሁ፥ እንዲህም አልሁት- “እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገርን ያደርጋል፤ የአባቴ የያሬድ የልጁ ወገኖች ከሰማይ በላይ ያለ የጌታን ቃል ተላልፈዋልና ይህን በራእይ ፈጽሜ አይቼ ነገርሁህ። 16 እነኋቸው፥ ኀጢአትን ይሠራሉ፤ ሥርዐቱንም ይተላለፋሉ፤ ከሴቶችም ጋር አንድ ሆኑ፤ ከእነርሱም ጋር ኀጢአትን ይሠራሉ፤ ከእነርሱም ሚስቶችን አገቡ፤ ከእነርሱም ልጆችን ወለዱ፤ በምድርም ሁሉ ላይ ታላቅ ጥፋት ይደረጋል። 17 የጥፋት ውኃም ይወርዳል፤ ታላቁም ጥፋት በአንዱ ዓመት ይደረጋል፤ ለእናንተም የተወለደው ልጅ ይህ ነው፤ እርሱ በምድር ላይ ይቀራል፤ ሦስቱ ልጆቹም ከእርሱ ጋራ ይድናሉ። 18 በምድር ላይ ሰው ሁሉ በሚሞትበት ጊዜ እርሱ ይድናል፤ ልጆቹም አርበኞችን ይወልዳሉ፥ እነዚህም ሥጋውያን እንጂ መንፈሳውያን አይደሉም። 19 ታላቅ መቅሠፍትም በምድር ላይ ይደረጋል፤ ምድርም ከጥፋት ሁሉ ትነጻለች። 20 “አሁንም ይህ የተወለደ ልጅ በእውነት የእርሱ ልጅ እንደ ሆነ ለልጅህ ለላሜህ ንገረው፤ እርሱም ቀሪ ይሆንላችኋልና ስሙን ኖኅ ብለህ ጥራው፤ በእርሱ ዘመን በምድር ላይ ትፈጸም ዘንድ ካላት ከኀጢአት ሁሉና ከዐመፅ ሁሉ የተነሣ ወደ ምድር ከምትመጣ ጥፋት እርሱና ልጆቹ ይድናሉ። ከዚህም በኋላ በምድር ላይ አስቀድማ ከተፈጸመችው ይልቅ ፈጽማ የምትበልጥ ዐመፅ ትደረጋለች፤ የቅዱሳንን ምሥጢራት ዐውቃለሁና። እርሱ እግዚአብሔር ገልጦልኛልና፥ አስረድቶኛልምና፤ በሰማይ ሰሌዳም አነበብሁ፤ አስተዋልሁም። 21 “እውነተኛ ትውልድ እስክትነሣ ድረስ ትውልድ ከትውልድ ይልቅ አብልጣ ትበድላለችና በእነርሱ ላይ የተጻፈውን አየሁ፤ በደልም ትጠፋለች፤ ኀጢአትም ከምድር ላይ ትርቃለች፤ በጎውም ነገር ሁሉ በእርሷ ላይ ይመጣል፤ አሁንም ይህ የተወለደው ልጅ በእውነት የእርሱ ልጅ ነውና፥ ሐሰትም አይደለምና ሄደህ ለልጅህ ለላሜህ ንገረው፤” ማቱሳላም የአባቱ የሄኖክን ነገር በሰማ ጊዜ ሥራውን ሁሉ በስውር አሳይቶታልና ነገሩን ሰምቶ ተመለሰ። 22 እርሱም ምድርን ከጥፋቷ ሁሉ ያሳርፋታልና የዚያን ልጅ ስም ኖኅ አለው። |