Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa

መጽሐፈ ሄኖክ 39 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)

1 የሰማይ ልጆች ሁሉ፥ ሰማይን ተረዷት፥ የልዑልንም ሥራ ሁሉ ተረዱ፤ ከእርሱም የተነሣ ፍሩ፤ በፊቱም ክፉ ነገርን አትሥሩ፤ ከእነርሱ የተነሣ ፍሩ።

2 የሰማይ ደጃፍን ቢዘጋ፥ ዝናቡንና ጠሉንም በምድር ላይ እንዳይወርድ በእናንተ ምክንያት ቢከለክል ምን ታደርጉ ዘንድ አላችሁ?

3 መዓቱንም በእናንተ ላይና በሥራችሁ ሁሉ ላይ ቢልክ እርሱን እናንተ የምትማልዱት አይደላችሁምን?

4 በቸርነቱ ላይ ታላላቅና የጸኑ ነገሮችን ትናገራላችሁና ሰላም የላችሁም።

5 ከማዕበሉ የተነሣ እንደሚታወኩ፥ መርከቦቻቸውም ከነፋሳት የተነሣ እንደሚነዋወጡና እንደሚጨነቁ በመርከብ የሚሄዱ ነገሥታትን አታይዋቸውምን?

6 መልካሙ ገንዘባቸውም ሁሉ ከእነርሱ ጋር ወደ ባሕር ይወጣልና ስለዚህ ይፈራሉ።

7 ባሕር ትውጣቸዋለችና፥ በውስጧም ይጠፋሉና በልቡናቸው በጎ ነገርን አያስቡም፤ ባሕሯ ሁሉ፥ ውኃዎችዋም ሁሉ፥ መነዋወጧም ሁሉ የልዑል ሥራ አይደለምን?።

8 እርሱ ሥራዋንና ውኃዎችዋን ሁሉ ወሰነ፥ ሁለመናዋንም በአሸዋ ገደበ።

9 በተግሣጹም ፈርታ ትደርቃለች፥ ዓሣዎችዋም ሁሉ ይሞታሉ፥ በውስጧም ያለ ሁሉ ይሞታል።

10 በምድር ያላችሁ እናንተ ኃጥኣን ግን አትፈሩትም፤ ሰማይንና ምድርን፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠረ እርሱ አይደለምን?

11 በየብስና በባሕር ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ ትምህርትንና ጥበብን የሰጠ ማን ነው? በመርከብ የሚሄዱ እነዚያ ባሕርን የሚፈሩ አይደለምን? ኃጥኣን ግን ልዑልን አይፈሩትም።

12 በእነዚያ ወራቶች አስጨናቂ እሳትን በላያችሁ ቢጨምር ወዴት ትሸሻላችሁ? በየትስ ትድናላችሁ?

13 ቃሉንም በእናንተ ላይ በሚያኖር ጊዜ የምትደነግጡና የምትፈሩ አይደለምን? ብርሃናትስ ሁሉ በታላቅ ፍርሀት የሚደነግጡና የሚታወኩ አይደለምን?

14 ምድርስ ሁላ በታላቅ ፍራት የምትደነግጥ፥ የምትንቀጠቀጥና የምትቸኩል አይደለምን?

15 መላእክትም ሁሉ የታዘዙትን ይፈጽማሉ፥ ከክብር ጌታም ፊት ሊሰወሩ ይወዳሉ።

16 የዓለም ልጆች ይርዳሉ፤ ይታወካሉም፤ እናንተም ኃጥኣን ለዘለዓለም የተረገማችሁ ናችሁ፥ ሰላምም የላችሁም።

17 እናንተ የጻድቃን ነፍሳት፥ አትፍሩ፤ እናንተም በእውነት የሞታችሁ፥ ተስፋ አድርጉ።

18 ነፍሳችሁ በታላቅ መከራና ጩኸት፥ በልቅሶና ኀዘን ወደ ሲኦል ስለ ወረደች አትዘኑ።

19 ሥጋችሁም በሕይወታችሁ እንደ ቸርነታችሁ አላገኘም፤ ነገር ግን ጊዜው ኃጥኣን የተባላችሁበት ነበር፥ የመርገምና የመከራም ጊዜ ነበር።

20 በምትሞቱበትም ጊዜ ኃጥኣን በእናንተ ላይ እንዲህ ይላሉ- “ጻድቃን እኛ እንደ ሞትን ሞቱ፥ በሥራቸውስ ጥቅማቸው ምንድን ነው?

21 እነሆ፥ በኀዘንና በመከራ እንደ እኛ ሞቱ፥ ከእኛስ ብልጫቸው ምንድን ነው? ከዛሬም ጀምሮ ተካከልን፥ ምንስ ያገኛሉ? ለዘለዓለምስ ምን ያያሉ? እነሆ፥ እነርሱ ሞተዋልና፥ ከዛሬም ጀምሮ ለዘለዓለም ብርሃንን አያዩምና።”

22 እናንተ ኃጥኣን፥ እንዲህ እላችኋለሁ- “መብልና መጠጥ ቅሚያና ኀጢአት፥ ሰውን መግፈፍና ገንዘብ ማጠራቀም፥ ደግ ዘመን ማየትም በቃችሁ።

23 ፍጻሜያቸው እንዴት ሰላም እንደ ሆነ ጻድቃንን አያችኋቸውን? እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ግፍ ሁሉ በእነርሱ ላይ አልተገኘምና።

24 ጠፉ፤ ተፈጥረውም እንዳልተፈጠሩ ሆኑ፥ ሰውነቶቻቸውም በመከራ ወደ መቃብር ወረዱ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos