መክብብ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔርን ስለ መፍራት 1 ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትሄድበት ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ የጠቢባንንም ትምህርት ለመስማት ቅረብ፤ ዳግመኛም ከሰነፎች ስጦታ መሥዋዕት አድርገህ ከመቀበል ተጠበቅ፤ እነርሱ መልካም ለመሥራት ዐዋቂዎች አይደሉምና። 2 እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ይሁን። 3 ሕልም በብዙ መከራ፥ እንዲሁም የሰነፍ ቃል በብዙ ነገር ይመጣልና። 4 ፈቃዱ አይደለምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፤ አንተ ግን እንደ ተሳልህ ስእለትህን ስጥ። 5 ተስለህ የማትፈጽም ከሆነ ባትሳል ይሻላል። 6 ለሥጋህ በደል አፍህን አትስጥ፥ በእግዚአብሔርም ፊት፥ “ባለማወቅ ነው” አትበል፤ እግዚአብሔር ስለ ቃልህ እንዳይቈጣ፥ የእጅህንም ሥራ እንዳያጠፋብህ፤ 7 ብዙ ሕልም፥ እንዲሁ ደግሞ ብዙ ቃል ከንቱ ነውና፤ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፈጽመህ ፍራ። ስለ ኑሮ ከንቱነት 8 ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለ ይጠብቅሃልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በሀገሩ ድሃ ሲበደል፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ብታይ በሥራው አታድንቅ። 9 የምድር ጥቅም ለሁሉ ነው፥ የንጉሥም ጥቅም በእርሻ ነው። 10 ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ብዙ እህልንም የሚወድድ እንዲሁ ነው፤ ይህም ከንቱ ነው። 11 ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፤ በዐይኑም ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? 12 ብዙ ወይም ጥቂት ቢበላ የአገልጋይ እንቅልፉ ጣፋጭ ነው፤ ብልጽግናን ያበዛ ሰውን ግን ይተኛ ዘንድ የሚተወው የለም። 13 ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ደዌ አለ፤ ለመከራው በባለቤቱ ዘንድ የተቈጠበች ባለጠግነት ናት። 14 ያችም ባለጠግነት በክፉ ንጥቂያ ትጠፋለች፤ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም። 15 ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፤ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለው ምንም የለም። 16 ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ደዌ ነው፥ እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳልና፥ ለሰውነቱ ለሚደክም ሰው ትርፉ ምንድን ነው? 17 ዘመኑ ሁሉ በጨለማ በልቅሶና በብዙ ብስጭት በደዌና በኀዘን ነውና። 18 እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር፦ ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ ዕድል ፈንታው ነውና። 19 እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና ዕድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ፥ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 20 እግዚአብሔር በልቡ ደስታ ስለሚያደክመው እርሱ የሕይወቱን ዘመን ሁሉ እጅግ አያስብም። |