1 ነገሥት 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰሎሞን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት ያደረገው ዝግጅት ( 2ዜ.መ. 2፥1-18 ) 1 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለአባቱ ለዳዊት በዘመኑ ሁሉ ወዳጁ ስለ ነበረ፥ ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ለመሆን እንደ ተቀባ ሰምቶ አገልጋዮቹን ወደ ሰሎሞን ላከ። 2 ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ ላከ፦ 3 “እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ጦርነት አባቴ ዳዊት ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ስም ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ። 4 አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ክፉም ነገር የሚያደርግ ጠላት የለብኝም። 5 እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፦ በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ። 6 አሁንም ከወገኔ እንደ ሲዶናውያን እንጨት መቍረጥ የሚያውቅ እንደሌለ ታውቃለህና የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ይቈርጡልኝ ዘንድ አገልጋዮችህን እዘዝ፤ አገልጋዮቼም ከአገልጋዮችህ ጋር ይሁኑ፤ የአገልጋዮችህንም ዋጋ እንደ ተናገርኸው ሁሉ እሰጥሃለሁ።” 7 ኪራምም የሰሎሞንን ቃል ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና፥ “በዚህ ታላቅ ሕዝብ ላይ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይመስገን” አለ። 8 ኪራምም እንዲህ ሲል ወደ ሰሎሞን ላከ፥ “የላክህብኝን ሁሉ ሰማሁ፤ ስለ ዝግባውና ስለ ጥዱ እንጨት ፈቃድህን ሁሉ አደርጋለሁ። 9 አገልጋዮቼ ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዱልሃል፤ እኔም በመርከብ አድርጌ በባሕር ላይ እያንሳፈፍሁ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ ድረስ አደርስልሃለሁ፤ በዚያም እፈታዋለሁ፤ አንተም ከዚያ ታስወስደዋለህ፤ አንተም ፈቃዴን ታደርጋለህ፤ ለቤተ ሰቦቼም ቀለብ የሚሆነውን ትሰጠኛለህ።” 10 እንዲሁም ኪራም የዝግባውንና የጥዱን እንጨት፥ የሚሻውንም ሁሉ ለሰሎሞን ሰጠው። 11 ሰሎሞንም ለኪራም ስለ ቤቱ ቀለብ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ፥ ሃያ ሺህም በቤት መስፈሪያ ጥሩ ዘይት ይሰጠው ነበር፤ ሰሎሞንም ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጥ ነበር። 12 እግዚአብሔርም እንደ ነገረው ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞንም መካከል ሰላም ነበረ፤ በመካከላቸውም ቃል ኪዳን አደረጉ። 13 ሰሎሞንም ከእስራኤል ሁሉ ገባሮቹን መርጦ አወጣ፤ የገባሮቹም ቍጥር ሠላሳ ሺህ ሰዎች ነበረ። 14 በየወሩም እያፈራረቀ ወደ ሊባኖስ ዐሥር ዐሥር ሺህ ይልክ ነበር፤ አንድ ወርም በሊባኖስ፥ ሁለት ወርም በቤታቸው ይቀመጡ ነበር። አዶኒራምም የገባሪዎች አለቃ ነበረ። 15 ለሰሎሞንም ሰባ ሺህ ተሸካሚዎች፥ ሰማንያ ሺህም በተራራው ላይ ድንጋይ የሚጠርቡ ጠራቢዎች ነበሩት። 16 ይኸውም በሰሎሞን ሥራ ላይ ከተሾሙት ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ የሠራተኞች አለቆች ሌላ ነው። 17 ንጉሡም የለዘቡ ታላላቅ ድንጋዮችንና ለቤቱም መሠረት ያልተጠረበውን ድንጋይ ያመጡ ዘንድ አዘዘ። 18 የሰሎሞንና የኪራም አናጢዎች፥ ጌባላውያንም ወቀሩአቸው፤ ለመሠረትም አኖሩአቸው፤ ቤቱንም ለመሥራት እንጨቱንና ድንጋዮቹን ሦስት ዓመት አዘጋጁ። |