1 ነገሥት 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አክዓብም ኤልያስ ያደረገውን፥ የሐሰት ነቢያትንም ሁሉ በሰይፍ እንደ ገደላቸው ለሚስቱ ለኤልዛቤል ነገራት። 2 ኤልዛቤልም፥ “አንተ ኤልያስ ከሆንህ እኔም ኤልዛቤል ከሆንሁ ነገ በዚህ ጊዜ ሰውነትህን ከእነዚህ እንደ አንዱ ሰውነት ባላደርጋት፥ አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ እንዲህም ይግደሉኝ” ብላ ወደ ኤልያስ ላከች። 3 ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፤ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፤ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ። 4 እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከደድሆ ዛፍ በታች ተቀመጠና፦ ይበቃኛል፤ አሁንም አቤቱ! እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ” ብሎ እንዲሞት ለመነ። 5 በደድሆውም ዛፍ በታች ተኛ፤ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና፥ “ተነሥተህ ብላ” አለው። 6 ከዚህ በኋላ ኤልያስ ተነሥቶ፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም፤ ጠጣም፤ ተመልሶም ተኛ። 7 የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፥ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ” አለው። 8 ተነሥቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚያም በበላው የምግብ ኀይል እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። 9 እዚያም ወዳለ ዋሻ ገባ፤ በዚያም አደረ፤ እነሆም፥ “ኤልያስ ሆይ! ምን አመጣህ?” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። 10 ኤልያስም፥ “ሁሉን ለሚገዛ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ” አለ። 11 እርሱም አለ፥ “ነገ ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም። እነሆም፥ እግዚአብሔር በዚያ አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዓለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። 12 ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔርም በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ እንደ ፉጨት ያለ ቀጭን ድምፅ ሆነ፤ በዚያም እግዚአብሔር ነበረ። 13 ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆም፥ “ኤልያስ ሆይ፥ ወደዚህ ለምን መጣህ?” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። 14 እርሱም፥ “ሁሉን ለሚገዛ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ” አለ። 15 እግዚአብሔርም አለው፥ “ሂድ፤ በመጣህበትም መንገድ በምድረ በዳ ወደ ደማስቆ ተመለስ፤ ከዚያም በደረስህ ጊዜ በሶርያ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ አዛሄልን ቅባው፤ 16 በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ የናሚሶን ልጅ ኢዩን ቅባው፤ በፋንታህም ነቢይ ይሆን ዘንድ የአቤልመሁላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው፤ 17 ከአዛሄልም ሰይፍ የሚያመልጠውን ሁሉ ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩም ሰይፍ የሚያመልጠውን ሁሉ ኤልሳዕ ይገድለዋል። 18 እኔም ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበዓል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ።” 19 ከዚያም ሄደ፤ የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በዐሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከዐሥራ ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት። 20 ኤልሳዕም በሬዎቹን ተወ፤ ኤልያስንም ተከትሎ ሄደ፥ “አባቴንና እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ ተወኝ፤ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ” አለው። እርሱም“ሂድና ተመለስ፤ ምን አድርጌልሃለሁ?” አለው። 21 ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፤ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፤ ለሕዝቡም ሰጣቸው፤ በሉም፤ እርሱም ተነሥቶ ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፤ ያገለግለውም ነበር። |