Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ምድያማውያንን መበቀል

1 እግዚአብሔር ሙሴን፣

2 “ለእስራኤላውያን ምድያማውያንን ተበቀልላቸው፤ ከዚያም ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ” አለው።

3 ስለዚህ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ምድያማውያንን ለመውጋት እንዲሄዱና ስለ እግዚአብሔርም እንዲበቀሏቸው ከሰዎቻችሁ ጥቂቶቹን ለጦርነት አዘጋጁ።

4 ከእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ አንዳንድ ሺሕ ሰው ለጦርነቱ ላኩ።”

5 ስለዚህ ከእስራኤል ጐሣዎች ተወጣጥቶ ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ ሺሕ፣ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሰው ለጦርነት ተዘጋጀ።

6 ሙሴም የቤተ መቅደሱን ንዋየ ቅድሳትና ምልክት መስጫ የሆኑትን መለከቶች ከያዘው ከካህኑ ከአልዓዛር ልጅ ከፊንሐስ ጋራ ከየነገዱ አንዳንድ ሺሕ ሰው ለጦርነት ላከ።

7 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከምድያም ጋራ ተዋጉ፤ ወንዱንም በሙሉ ፈጁት፤

8 ከተገደሉትም መካከል ዐምስቱ የምድያም ነገሥታት ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ ይገኙባቸዋል፤ የቢዖርን ልጅ በለዓምንም በሰይፍ ገደሉት።

9 ከዚያም እስራኤላውያን የምድያማውያንን ሴቶችና ሕፃናት ማረኩ፤ የቀንድ ከብቶቻቸውን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን ሁሉ ነዱ፤ ሀብታቸውንም በሙሉ ወሰዱ።

10 ምድያማውያኑ የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም በሙሉ አቃጠሉ።

11 ሰውና እንስሳትን ጨምሮ የማረኩትንና የዘረፉትን ሁሉ እንዳለ አጋዙት።

12 የማረኳቸውን ሰዎች፣ የነዷቸውን እንስሳትና የዘረፉትን ሀብት በሙሉ፣ ከኢያሪኮ ማዶ፣ በዮርዳኖስ አጠገብ፣ በሞዓብ ወዳለው፣ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር እንዲሁም መላው የእስራኤላውያን ማኅበር ወዳሉበት ሰፈራቸው አመጧቸው።

13 ሙሴ፣ ካህኑ አልዓዛርና የማኅበረ ሰቡ መሪዎች በሙሉ ሊቀበሏቸው ከሰፈር ወጡ።

14 ሙሴም ከጦርነት በተመለሱት በሰራዊቱ አዛዦች፣ ማለትም በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።

15 ሙሴም እንዲህ አላቸው፤ “ሴቶችን ሁሉ እንዴት በሕይወት ትተዉአቸዋላችሁ?

16 የበለዓምን ምክር ተቀብለው በፌጎር በተፈጸመው ድርጊት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር እንዲመለሱና የእግዚአብሔርም ሕዝብ እንዲቀሠፍ ያደረጉት እነርሱ ናቸው።

17 አሁንም ወንዶቹን ልጆች ሁሉ፣ ወንድ ያወቁትንም ሴቶች በሙሉ ግደሏቸው፤

18 ነገር ግን ወንድ ያላወቁትን ልጃገረዶች ሁሉ ለራሳችሁ አስቀሯቸው።

19 “ከእናንተ መካከል ሰው የገደለ ወይም የተገደለውን የነካ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ይቈይ። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና ምርኮኞቻችሁን አንጹ።

20 ማንኛውንም ልብስ እንዲሁም ከቈዳ፣ ከፍየል ጠጕር ወይም ከዕንጨት የተሠራ ማንኛውንም ነገር አንጹ።”

21 ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ወደ ጦርነት ሄደው የነበሩትን ወታደሮች እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው የሕጉ ሥርዐት ይህ ነው፤

22 ወርቅ፣ ብር፣ ናስ፣ ብረት፣ ቈርቈሮ፣ እርሳስ

23 እንዲሁም እሳትን መቋቋም የሚችል ማንኛውም ነገር በእሳት ውስጥ ማለፍ አለበት፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል፤ ይህም ሆኖ መንጻት አለበት። እሳትን መቋቋም የማይችል ማንኛውም ነገር በዚሁ ውሃ ውስጥ ማለፍ አለበት።

24 በሰባተኛው ቀን ልብሳችሁን ዕጠቡ፤ ትነጻላችሁም፤ ከዚያም ወደ ሰፈር መግባት ትችላላችሁ።”


ምርኮን መከፋፈል

25 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

26 “አንተ፣ ካህኑ አልዓዛርና በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያሉት የየቤተ ሰቡ አለቆች ሆናችሁ የተማረከውን ሕዝብና እንስሳት ሁሉ ቍጠሩ።

27 ምርኮውንም ለሁለት ከፍላችሁ በጦርነቱ ለተካፈሉት ወታደሮችና ለቀረው ማኅበረ ሰብ አከፋፍሉት።

28 በጦርነቱ ከተካፈሉት ወታደሮች ድርሻ ላይ፣ ከሰውም ሆነ ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ከየዐምስት መቶው አንዱን ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ።

29 ይህንም ግብር ከድርሻቸው ላይ ወስደህ የእግዚአብሔር ፈንታ በማድረግ ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው።

30 ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ደግሞ ከሰውም ይሁን ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ፣ ከፍየል ወይም ከሌሎች እንስሳት ከየዐምሳው አንዳንድ መርጠህ፣ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ስጣቸው።”

31 ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

32 ወታደሮቹ ማርከው ከወሰዱለት ምርኮ ውስጥ የቀረው ይህ ነበር፤ ስድስት መቶ ሰባ ዐምስት ሺሕ በግ፣

33 ሰባ ሁለት ሺሕ የቀንድ ከብት፣

34 ስድሳ አንድ ሺሕ አህያ

35 ወንድ ያላወቁ ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሴቶች።

36 በጦርነቱ ላይ የነበሩት ወታደሮች እኩሌታ ድርሻ ይህ ነበር፤ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ በግ፣

37 ከእነዚህም በጎችና ፍየሎች ለእግዚአብሔር የተሰጠ ግብር ስድስት መቶ ሰባ ዐምስት ነበር።

38 ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር የተሰጠው ግብር ሰባ ሁለት ነበር።

39 ሠላሳ ሺሕ ዐምስት መቶ አህያ፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር የተሰጠው ግብር ስድሳ አንድ ነበር።

40 ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር የተሰጠው ግብር ሠላሳ ሁለት ነበር።

41 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእግዚአብሔር ድርሻ የሆነውን ግብር ለካህኑ አልዓዛር ሰጠው።

42 ሙሴ ከዘመቱት ሰዎች የለየው የእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ማለትም፣

43 የማኅበረ ሰቡ ድርሻ ይህ ነበር፤ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ በግ፣

44 ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣

45 ሠላሳ ሺሕ ዐምስት መቶ አህያ፣

46 ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው።

47 ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ላይ፣ ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከየዐምሳው ሰውና እንስሳ አንዳንድ መርጦ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጣቸው።

48 ከዚያም በኋላ በሰራዊቱ ክፍሎች ላይ የተሾሙት የሻለቆችና የመቶ አለቆች ወደ ሙሴ ቀርበው፣

49 እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ በእጃችን ሥር ያሉትን ወታደሮች ቈጥረናል፤ አንድም የጐደለ የለም።

50 ስለዚህ እያንዳንዳችን ያገኘነውን የወርቅ ጌጣጌጥ፣ የእግር ዐልቦዎች፣ የእጅ አንባሮች፣ የጣት ቀለበቶች፣ የጆሮ ጕትቻዎችና የዐንገት ሐብሎች በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ እንዲሆነን መባ አድርገን ለእግዚአብሔር አምጥተናል።”

51 ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በጌጣጌጥ መልክ የተሠራውን ወርቅ ሁሉ ተቀበሏቸው።

52 ሙሴና አልዓዛር ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ በመቀበል ስጦታ አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀረቡት ወርቅ ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐምሳ ሰቅል መዘነ።

53 እያንዳንዱም ወታደር ለራሱ የወሰደው ምርኮ ነበረው።

54 ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤላውያን መታሰቢያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን አመጡት።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos