ዘኍል 16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን 1 የሌዊ ልጅ፣ የቀዓት ልጅ፣ የይስዓር ልጅ የሆነው ቆሬ፣ ከሮቤልም ነገድ የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን እንዲሁም የፍሌት ልጅ ኦን በክፋት ተነሣሥተው፣ 2 ሙሴን ተቃወሙት። ከእነዚህም ጋራ ታዋቂ የማኅበረ ሰቡ መሪዎች የሆኑና በጉባኤ አባልነት የተመረጡ ሁለት መቶ ዐምሳ እስራኤላውያን ዐብረው ነበሩ። 3 እነዚህም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ግንባር ፈጥረው በመምጣት፣ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም? የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋራ ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ የምትታበዩት ለምንድን ነው?” አሏቸው። 4 ሙሴም ይህን ሲሰማ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ 5 ቆሬንና ተከታዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የርሱ የሆነውና የተቀደሰው ማን መሆኑን እግዚአብሔር ጧት ያሳውቃል፤ ወደ ራሱም ያመጣዋል፤ የሚመርጠውን ሰው ወደ ራሱ እንዲቀርብ ያደርገዋል። 6 ቆሬ፣ አንተና ተከታዮችህ ሁሉ እንዲህ አድርጉ፤ ጥናዎችን ውሰዱ፤ 7 በማግስቱም በእግዚአብሔር ፊት እሳትና ዕጣን ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔር የሚመርጠውም ያ ሰው ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ናችሁ።” 8 ደግሞም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፤ “እናንተ ሌዋውያን ስሙ፤ 9 የእስራኤል አምላክ እናንተን ከቀሩት እስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ መለየቱና በእግዚአብሔር ማደሪያ አገልግሎት እንድትፈጽሙ ወደ ራሱ ማቅረቡ፣ እንድታገለግሏቸውም በማኅበረ ሰቡ ፊት እንድትቆሙ ማድረጉ አይበቃችሁምን? 10 አንተንና ከአንተም ጋራ ወገኖችህ የሆኑትን ሌዋውያንን ሁሉ ወደ ራሱ አቅርቧችኋል፤ እናንተ ግን የክህነቱንም ሥራ ደርባችሁ ለመያዝ ይኸው ትሯሯጣላችሁ። 11 አንተና ተከታዮችህ ሁሉ አባሪ ተባባሪ ሆናችሁ የተነሣችሁት በእግዚአብሔር ላይ ነው፤ ለመሆኑ ታጕረመርሙበት ዘንድ አሮን ማነው?” 12 ከዚያም ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን አስጠራቸው፤ እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፤ “እኛ አንመጣም! 13 በምድረ በዳ ልትገድለን ማርና ወተት ከምታፈሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህም? አሁን ደግሞ በእኛ ላይ ጌታ መሆን ያምርሃል? 14 ከዚህም በቀር አንተ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ምድር አላመጣኸንም፤ ወይም ዕርሻዎችንና የወይን ተክል ቦታዎች አላወረስኸንም። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ታወጣለህን? በጭራሽ አንመጣም!” 15 ሙሴም በጣም ተቈጣ፤ እግዚአብሔርንም “ቍርባናቸውን አትቀበል፤ እኔ ከእነዚህ ሰዎች የወሰድሁት አንድ አህያ እንኳ የለም፤ አንዳቸውንም አልበደልሁም” አለ። 16 ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፤ “አንተና ተከታዮችህ እንዲሁም አሮን ነገ በእግዚአብሔር ፊት ትቀርባላችሁ። 17 እያንዳንዱም ሰው ጥናውን ይወስዳል፤ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ዐምሳ ጥናዎች ይሆናሉ፤ በዚያም ላይ ዕጣን ጨምሮ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል፤ አንተና አሮንም ጥናዎቻችሁን እንደዚሁ ታቀርባላችሁ።” 18 እያንዳንዱ ሰው ጥናውን በመያዝ ፍም አድርጎበት፣ ዕጣን ጨምሮበት ከሙሴና ከአሮን ጋራ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ። 19 ቆሬም እነርሱን በመቃወም ተከታዮቹን ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ክብር ለመላው ማኅበር ተገለጠ። 20 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 21 “ሁሉንም በአንድ ጊዜ እንዳጠፋቸው እናንተ ከዚህ ማኅበር ተለዩ።” 22 ሙሴና አሮን ግን በግንባራቸው ተደፍተው፣ “የሥጋ ለባሽ ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆንህ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንድ ሰው ኀጢአት በሠራ በመላው ማኅበር ላይ ትቈጣለህን?” ሲሉ ጮኹ። 23 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 24 “ማኅበሩን ‘ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ራቁ’ በላቸው።” 25 ሙሴ ተነሥቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት። 26 እርሱም፣ “ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳን ራቁ የእነርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ፤ አለዚያ በእነርሱ ኀጢአት ሁሉ እናንተም ትጠፋላችሁ” ሲል ማኅበሩን አስጠነቀቀ። 27 ስለዚህ እነርሱ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን ራቁ። ዳታንና አቤሮን ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃናቶቻቸው ጋራ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ነበር። 28 ሙሴም እንዲህ አለ፤ “እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዳደርግ እግዚአብሔር እንደ ላከኝና ከራሴም እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ፤ 29 እነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው አሟሟት የሚሞቱ ቢሆኑና በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሰው ብቻ የሚደርስባቸው ከሆነ፣ እኔን እግዚአብሔር አልላከኝም። 30 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ፈጽሞ አዲስ የሆነ ነገር አምጥቶ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥና በሕይወታቸው ወደ መቃብር ቢወርዱ፣ ሰዎቹ እግዚአብሔርን የናቁ መሆናቸውን የምታውቁት ያን ጊዜ ነው።” 31 ይህን ሁሉ ተናግሮ እንደ ጨረሰ የቆሙባት ምድር ተሰነጠቀች፤ 32 አፏንም ከፍታ ሰዎቹን ከነቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም የቆሬን ሰዎች በሙሉ፣ ንብረታቸውንም ሁሉ ዋጠች። 33 እነርሱም ካላቸው ከማናቸውም ነገር ጋራ ከነሕይወታቸው ወደ መቃብር ወረዱ፤ ምድሪቱም በላያቸው ተከደነችባቸው፤ ጠፉ፤ ከማኅበረ ሰቡም ተወገዱ። 34 ከጩኸታቸውም የተነሣ በአካባቢያቸው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ምድሪቱ እኛንም እኮ ልትውጠን ነው” ብለው ሸሹ። 35 እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ የሚያጥኑትን ሁለት መቶ ዐምሳ ሰዎች በላቻቸው። 36 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 37 “ጥናዎቹ የተቀደሱ ናቸውና ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ ወስደህ በውስጣቸው ያለውን ፍም አርቆ እንዲደፋ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር ንገረው፤ 38 እነዚህም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ኀጢአት የሠሩ ሰዎች ጥና ናቸው፤ ጥናዎቹም በእግዚአብሔር ፊት የቀረቡና የተቀደሱ በመሆናቸው ለመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጥቅጠህ አሣሣቸው፤ እነዚህም ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያ ይሁኑ።” 39 ከዚህ የተነሣም ካህኑ አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች አምጥተዋቸው የነበሩትን የናስ ጥናዎች ሰብስቦ የመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጠቀጣቸው፤ 40 ይህን ያደረገውም፣ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት ነው፤ ይህም ከአሮን ዘር በቀር ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ዕጣን እንዳያጥን አለዚያ ግን፣ እንደ ቆሬና እንደ ተከታዮቹ እንደሚሆን ለእስራኤላውያን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነበር። 41 በማግስቱም መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ፣ “እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ። 42 ማኅበሩም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን ዘወር ሲሉ ደመና ድንኳኑን በድንገት ሸፍኖት አዩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ። 43 ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ሄዱ። 44 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 45 “በቅጽበት አጠፋቸዋለሁና ከዚህ ማኅበር ራቅ” እነርሱም በግንባራቸው ተደፉ። 46 ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ቍጣ ወጥቶ መቅሠፍት ጀምሯልና ጥናውን ወስደህ ዕጣን በመጨመር ከመሠዊያው እሳት አድርግበት፤ ፈጥነህም ወደ ማኅበሩ ሄደህ አስተስርይላቸው” አለው። 47 ስለዚህ አሮን፣ ሙሴ በነገረው መሠረት ወደ ማኅበሩ መካከል ሮጦ ገባ፤ መቅሠፍቱም ቀደም ብሎ በሕዝቡ መካከል መስፋፋት ጀምሮ ነበር፤ ሆኖም አሮን ዕጣኑን ዐጥኖ አስተሰረየላቸው። 48 እርሱም በሕይወት ባሉትና በሞቱት መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ። 49 ይሁን እንጂ በቆሬ ምክንያት የሞቱትን ሳይጨምር ዐሥራ አራት ሺሕ ሰባት መቶ ሰዎች ተቀሥፈው ሞቱ። 50 ከዚያም መቅሠፍቱ ቆመ፤ አሮንም ሙሴ ወዳለበት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.