ማርቆስ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢየሱስ ሽባ ፈወሰ 2፥3-12 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥2-8 ፤ ሉቃ 5፥18-26 1 ኢየሱስ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም እንደ ተመለሰ፣ ወደ ቤት መግባቱን ሕዝቡ ሰማ። 2 ስለዚህ ከበሩ ውጭ እንኳ ሳይቀር ስፍራ እስኪታጣ ድረስ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ሰበከላቸው። 3 ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። 4 ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ እርሱ ወዳለበት ሊያቀርቡት ስላልቻሉ፣ የቤቱን ጣራ እርሱ ባለበት በኩል ነድለው ቀዳዳ በማበጀት ሽባው የተኛበትን ዐልጋ በዚያ አወረዱ። 5 ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። 6 በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ስለዚህ ነገር በልባቸው እያሰላሰሉ፣ 7 “ይህ ሰው እንዴት እንዲህ ይላል? በአምላክ ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ እኮ ነው! ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” ብለው አሰቡ። 8 ኢየሱስም ወዲያው የሚያስቡትን በመንፈሱ ተረድቶ፣ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ? 9 ሽባውን፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና፣ ‘ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀልላል? 10 ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ሽባውን፣ 11 “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። 12 እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ዐልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ በስፍራው የነበሩትም ሁሉ በሁኔታው በመደነቅ፣ “የዚህ ዐይነት ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም!” በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ። የሌዊ መጠራት 2፥14-17 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥9-13 ፤ ሉቃ 5፥27-32 13 ኢየሱስም ዳግም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጣ፤ ሕዝቡም በብዛት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም አስተማራቸው። 14 በዚያም ሲያልፍ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መሰብሰቢያው ስፍራ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። 15 በሌዊም ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች ተከትለውት ስለ ነበር፣ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ዐብረው ይመገቡ ነበር። 16 የፈሪሳውያን ጸሐፍት ከኀጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋራ ሲበላ ባዩት ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋራ ለምን ይበላል?” ሲሉ ጠየቋቸው። 17 ኢየሱስም የሚናገሩትን ሰምቶ፣ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” አላቸው። ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ 2፥18-22 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥14-17 ፤ ሉቃ 5፥33-38 18 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎችም መጥተው ኢየሱስን፣ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት። 19 ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ዕድምተኞቹ ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ሊጾሙ አይችሉም፤ 20 ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያም ጊዜ ይጾማሉ። 21 “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ቍራጭ ጨርቅ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፣ አዲሱ ጨርቅ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሰፋል። 22 እንዲሁም አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ የሚያስቀምጥ የለም፤ ይህ ከተደረገማ የወይን ጠጁ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም አቍማዳውም ይበላሻሉ። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ መቀመጥ ያለበት በአዲስ አቍማዳ ነው።” ኢየሱስ የሰንበት ጌታ ነው 3፥1-6 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥9-14 ፤ ሉቃ 6፥6-11 23 በሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ሲያልፍ፣ ዐብረውት በመጓዝ ላይ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። 24 ፈሪሳውያንም፣ “እነሆ፤ በሰንበት ቀን ለምን ያልተፈቀደውን ነገር ያደርጋሉ?” ሲሉ ጠየቁት። 25 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት በተራበና የምግብ ፍላጎት በጸናበት ጊዜ ዐብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋራ ያደረገውን አላነበባችሁምን? 26 በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፣ ካህናት ብቻ እንዲበሉት የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ለርሱም ሆነ ዐብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” 27 ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም፤ 28 ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.