መዝሙር 75 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም(ለመዘምራን አለቃ አታጥፋ በሚል የዜማ ቃና የአሳፍ መዝሙር) የእግዚአብሔር ፈራጅነት 1 አምላክ ሆይ፥ እናመሰግንሃለን፤ አንተ ወደ እኛ ስለ ቀረብክ ለስምህ ምስጋና እናቀርባለን፤ ስላደረግኸው ድንቅ ሥራ እንናገራለን። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ፍርድ የምሰጥበትን ጊዜ ወስኛለሁ፤ በዚያን ጊዜ በትክክል እፈርዳለሁ። 3 ምድር ስትናወጥ፥ በውስጥዋ ያሉትም ሕያዋን ፍጥረቶች ቢንቀጠቀጡም እንኳ እኔ የምድርን መሠረት አጸናለሁ። 4 ትዕቢተኞችን ‘አትታበዩ’ ክፉዎችን ‘አታምፁ’ እላቸዋለሁ፤ 5 በእግዚአብሔር ላይ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ ወይም በትዕቢት አትናገር።” 6 ፍርድ ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ፥ ወይም ከምድረ በዳ አይመጣም፤ 7 በአንዱ ላይ የሚፈርድ፥ ሌላውን ነጻ የሚያወጣ፥ ትክክለኛ ፈራጅ እግዚአብሔር ነው። 8 እግዚአብሔር የተቀመመ ወይን ጠጅ የተሞላበትን ጽዋ በእጁ ይዞአል፤ በቊጣው ሲያፈስሰው ክፉዎች ሁሉ ይጠጡታል፤ እስከ መጨረሻው ጠብታ ድረስ ይጨልጡታል። 9 እኔ ግን ስለ ያዕቆብ አምላክ ከመናገር ስለ ክብሩም ከመዘመር ከቶ አልቈጠብም። 10 እርሱ የክፉዎችን ኀይል ይሰብራል፤ የጻድቃን ኀይል ግን እየጨመረ ይሄዳል። |