Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 59 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔርን ጠባቂነት የሚገልጥ ጸሎት

1 አምላክ ሆይ! ከጠላቶቼ አድነኝ፤ በእኔ ላይ ከሚነሡ ሰዎችም ጠብቀኝ።

2 ከነዚያ ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤ ከነዚያም ነፍሰ ገዳዮች ታደገኝ።

3 እንዴት እንደ ሸመቁብኝ ተመልከት! እግዚአብሔር ሆይ! ምንም በደልና ኃጢአት ሳልሠራ ዐመፀኞች ሰዎች በእኔ ላይ ያሤራሉ።

4 ምንም በደል ሳልሠራ ሊያጠቁኝ ተዘጋጅተዋል፤ ይህን ተመልከትና ተነሥተህ እርዳኝ።

5 አንተ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነህ፤ ሕዝቦችን ለመቅጣት ተነሥ፤ ክፉ ከዳተኞችን ያለ ምሕረት ቅጣቸው።

6 እነርሱ በከተማይቱ ውስጥ እንደ ውሻ እያላዘኑ ሲልከሰከሱ ውለው ወደ ማታ ይመለሳሉ።

7 ከአፋቸው የሚወጣውን ተመልከት፤ ምላሳቸው እንደ ተሳለ ሰይፍ ነው፤ ነገር ግን ማንም የሚሰማቸው አይመስላቸውም።

8 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን በእነርሱ ላይ ትስቃለህ፤ አሕዛብን ሁሉ ትንቃለህ።

9 አምላክ ሆይ! መጠጊያዬ ስለ ሆንክ በአንተ እተማመናለሁ።

10 አምላኬ በዘለዓለማዊ ፍቅሩ በፊቴ ይሄዳል፤ ጌታዬ፥ ጠላቶቼን በንቀት ዐይን እንድመለከታቸው ያደርገኛል።

11 መከታችን እግዚአብሔር ሆይ! ወገኖቼ የአንተን ተበቃይነት እንዳይረሱ፥ አትግደላቸው፤ ነገር ግን በኀይልህ በትናቸው፤ አዋርዳቸውም።

12 ከአንደበታቸው ኃጢአት አይጠፋም፤ ንግግራቸው ሁሉ ኃጢአት የሞላበት ነው፤ እነርሱ ስለሚራገሙና ስለሚዋሹ በትዕቢታቸው ይያዙ!

13 በቊጣህ አጥፋቸው፤ ፈጽመህም ደምስሳቸው፤ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እስራኤልን እንደሚያስተዳድርና ግዛቱም በምድር ሁሉ እንደ ተንሰራፋ፥ ሰው ሁሉ ያውቃል።

14 ጠላቶቼ በከተማይቱ ውስጥ እንደ ውሻ እያላዘኑ ሲልከሰከሱ ውለው፥ ወደ ማታ ይመለሳሉ።

15 እነርሱ ምግብ ለማግኘት እንደሚቅበዘበዙና በቂ ምግብ ካላገኙም እንደሚያላዝኑ ውሾች ናቸው።

16 በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና ምሽጌ ስለ ሆንክ ስለ ኀያልነትህ ክብርና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ዘወትር በማለዳ እዘምራለሁ።

17 አምላክ ሆይ! አንተ ብርታቴ ነህ፤ አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ ዘለዓለማዊ ፍቅርህንም ታሳየኛለህ፤ ስለዚህ የምስጋና መዝሙር አቀርብልሃለሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos