Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 45 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የፍቅር ቅኔ

1 ልቤ መልካም ርእስን ያፈልቃል፤ ጽሑፌም የሚያተኲረው በንጉሡ ላይ ነው፤ አንደበቴም እንደ መልካም ጸሐፊ ብዕር ነው።

2 አንተ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ የተዋብክ ነህ፤ ንግግርህም ሞገስ የሞላበት ነው፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ባርኮሃል።

3 በክብርና በግርማ የተሞላህ ኀያል ንጉሥ ሆይ፥ ሰይፍህን ታጠቅ።

4 ስለ እውነትና ስለ ፍትሕ ግርማን ተጐናጽፈህ ድል ለማድረግ ገሥግሥ፤ ኀይልህም ታላላቅ ድሎችን ያስገኛል።

5 ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፤ የጠላቶችህንም ልብ ይወጋሉ፤ መንግሥታትም ተሸንፈው በእግርህ ሥር ይወድቃሉ።

6 አምላክ ሆይ! ዙፋንህ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የጸና ነው። በትረ መንግሥትህም የፍትሕ በትረ መንግሥት ነው።

7 አንተ መልካሙን ነገር ትወዳለህ፤ ክፉውን ነገር ትጠላለህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ መረጠህ፤ ከሌሎች ነገሥታትም ይበልጥ የደስታን ዘይት ቀባህ።

8 ከከርቤ፥ ከእሬትና ከብርጒድ የተቀመመ ሽቶ በንጉሣዊ ልብስህ ላይ ተርከፍክፎአል፤ በዝሆን ጥርስ በተጌጠው ቤተ መንግሥትህም የበገና ሙዚቃ ቃና ያስደስትሃል።

9 በቤተ መንግሥትህ ከሚገኙት ወይዛዝርት መካከል፥ የነገሥታት ሴቶች ልጆች ይገኛሉ፤ ንግሥቲቱም በንጹሕ ወርቅ ያሸበረቀ ጌጠኛ ልብስ ተጐናጽፋ ከዙፋንህ በስተቀኝ ቆማለች።

10 አንቺ ልጄ ሆይ! የምልሽን ስሚ፤ ቃሌንም አድምጪ፤ ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ።

11 በውበትሽ ንጉሡ ይወድሻል፤ ሆኖም ጌታሽ በመሆኑ እጅ በመንሣት አክብሪው።

12 የጢሮስ ሰዎች ስጦታ ያመጡልሻል፤ ሀብታሞችም ደጅ ይጠኑሻል።

13 በቤተ መንግሥት የተቀመጠችው ልዕልት አጊጣለች ልብስዋም በወርቅ አሸብርቆአል።

14 ጌጠኛ ልብስዋንም ተጐናጽፋ ወደ ንጉሡ ትቀርባለች፤ ሚዜዎችዋ የሆኑ ልጃገረዶችም ያጅቡአታል፤

15 በደስታና በሐሤትም አብረው ወደ ንጉሡ ቤት ይገባሉ።

16 ንጉሥ ሆይ! በቀድሞ አባቶችህ ተተክተው የሚነግሡ ብዙ ልጆች ይኖሩሃል፤ አንተም በምድር ሁሉ ላይ ልዑላን አድርገህ ትሾማቸዋለህ።

17 እኔ በየትውልዱ ዝናህን እገልጣለሁ፤ ስለዚህ ሕዝቦች ሁሉ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ያመሰግኑሃል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos