Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 38 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በጭንቅ ጊዜ የሚቀርብ ጸሎት

1 እግዚአብሔር ሆይ! በቊጣህ አትገሥጸኝ፤ በኀይለኛ ቊጣህም አትቅጣኝ።

2 በፍላጻዎችህ ወግተኸኛል፤ በብርቱ እጅህም መተኸኛል።

3 ከቊጣህ የተነሣ ሥጋዬ ደኅንነት የለውም። በኃጢአቴም ምክንያት መላ ሰውነቴ ጤንነት የለውም።

4 በደሌ በራሴ ላይ ተጭኖአል፤ እርሱም ለመሸከም ከምችለው በላይ ነው።

5 በሞኝነት ካደረግሁት ስሕተት የተነሣ ቊስሌ በስብሶ ይሸታል።

6 ጐበጥኩ፤ እጅግም እያጐነበስኩ ሄድኩ፤ ቀኑን ሙሉ በትካዜ አሳለፍኩ።

7 ትኲሳት ወገቤን እያቃጠለው ነው፤ ሁለመናዬም ጤና አጣ።

8 ደክሜአለሁ፤ ፈጽሞም ደቅቄአለሁ፤ ከልቤ ጭንቀት የተነሣም እቃትታለሁ።

9 ጌታ ሆይ! የልቤን ፍላጎት ሁሉ ታውቃለህ፤ የእኔም መቃተት ለአንተ ምሥጢር አይደለም።

10 ልቤ በፍጥነት ይመታል፤ ኀይሌም ደክሞአል፤ ዐይኖቼም ብርሃን አጥተዋል።

11 ወዳጆቼና ጓደኞቼ ሕመሜን ተጸየፉ፤ ዘመዶቼም ከእኔ ራቁ፤

12 ሊገድሉኝ የሚፈልጉ ወጥመድ ይዘረጉብኛል፤ ሊጐዱኝ የሚያቅዱ ሊያጠፉኝ ይዝታሉ፤ በእኔም ላይ ቀኑን ሙሉ ያሤራሉ።

13 እኔ ግን ሊሰማ እንደማይችል ደንቆሮ፥ ለመናገር እንደማይችል ድዳ ሰው ነኝ።

14 በእውነትም እንደማይሰማና መልስ ለመስጠት እንደማይችል ሰው ሆኜአለሁ።

15 እግዚአብሔር ሆይ! በአንተ እተማመናለሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! አንተም መልስ ትሰጠኛለህ።

16 “ጠላቶቼ እኔን በንቀት ዐይን እንዲመለከቱኝ ወይም እግሬን ሲያዳልጠው ራሳቸውን ከፍ እንዲያደርጉ አታድርግ!” ብዬ እለምናለሁ።

17 ፋታ ከማይሰጠው ሕመሜ የተነሣ ተዝለፍልፌ ልወድቅ ተቃርቤአለሁ።

18 በደሌን እናዘዛለሁ፤ ኃጢአቴም አስጨንቆኛል።

19 ያለ ምክንያት ጠላት የሆኑብኝ ኀያላን ናቸው፤ በስሕተትም የሚጠሉኝ ብዙዎች ናቸው።

20 እኔ ደግ ሥራ በመሥራቴ በመልካም ፈንታ ክፉ የሚመልሱልኝ፤ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሥተዋል።

21 እግዚአብሔር ሆይ! አትተወኝ፤ አምላኬ ሆይ! ከእኔ አትራቅ።

22 አዳኜ አምላኬ ሆይ! ፈጥነህ እርዳኝ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos