መዝሙር 122 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ኢየሩሳሌም የቀረበ ውዳሴ 1 “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ!” ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። 2 ኢየሩሳሌም ሆይ! በበሮችሽ ገብተን በውስጥ ቆመናል። 3 ኢየሩሳሌም እርስ በርስዋ ተጠጋግታና ተጠናክራ የተሠራች ከተማ ናት። 4 በትእዛዙ መሠረት ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ የሚሰበሰቡት ወደዚህች ከተማ ነው። 5 ከዳዊት ዘር የነገሡ ሁሉ ሕዝባቸውን ለመዳኘት በዚህች ከተማ ይቀመጡ ነበር። 6 በኢየሩሳሌም ከተማ ሰላም እንዲሆን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “የሚወዱሽ ሁሉ ይበልጽጉ፤ 7 በቅጥሮችሽ ውስጥ ሰላም ይሁን፤ በቤተ መንግሥትሽም ውስጥ ጸጥታ ይኑር።” 8 በዘመዶቼና በወዳጆቼ ምክንያት ኢየሩሳሌምን “ሰላም ከአንቺ ጋር ይሁን!” እላታለሁ። 9 ኢየሩሳሌም ሆይ! በአምላካችን በእግዚአብሔር ቤት ምክንያት ለአንቺ መልካም ነገር እንዲሆንልሽ እመኛለሁ። |