Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ምሳሌ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ልጄ ሆይ! ቃሌን ጠብቅ፤ ትእዛዞቼንም በልብህ ውስጥ አኑር።

2 በሕይወት እንድትኖር ትእዛዞቼን ጠብቅ፤ የማስተምርህንም ሁሉ እንደ ዐይንህ ብሌን ጠብቅ፤

3 እንደ ጣትህ ቀለበት ጠብቃቸው፤ በልብህም ሰሌዳ ቅረጻቸው።

4 ጥበብን እንደ እኅትህ፥ ማስተዋልንም እንደ ቅርብ ወዳጅህ አድርገህ ቊጠራቸው።

5 እነርሱ ከአመንዝራ ሴት እንድትርቅና ከሌላ ሰው ሚስት አሳሳች ቃል እንድትጠበቅ ያደርጉሃል።


የአመንዝራ ሴት አታላይነት

6 ከዕለታት አንድ ቀን በቤቴ መስኮት ወደ ውጪ እመለከት ነበር፤

7 ዕውቀት ከጐደላቸው ሰዎች መካከል ወጣቶችን ተመለከትኩ፤ ከእነርሱም መካከል አስተሳሰብ የጐደለው አንድ ወጣት አየሁ።

8 አንዲት ሴት በምትኖርበት ቤት አጠገብ ባለው መንገድ ማእዘን ያልፍ ነበር፤ ወደ ቤትዋም አቅጣጫ ይራመድ ነበር፤

9 ይህንንም ያደርግ የነበረው ወደ ማታ ጊዜ ጨለምለም ሲል ነበር፤

10 ከዚያም በኋላ ሴትዮዋ ወጣችና አገኘችው፤ አለባበስዋም ሴትኛ ዐዳሪ መሆኗን ያመለክት ነበር፤ ሰውንም የምታስትበት ዕቅድ ነበራት።

11 እርስዋ ደፋርና ኀፍረተቢስ ሴት ነበረች፤ በቤትዋ መቀመጥ ስለማያስደስታት ዘወትር ትዞራለች፤

12 በየማእዘኑ፥ በየመንገዱና በየገበያ ስፍራ እየቆመች ትጠባበቃለች።

13 ያንን ወጣት ዕቅፍ አድርጋ ሳመችው፤ ያለ ኀፍረት እንዲህ አለችው፦

14 “እኔ መሥዋዕት ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ የስእለቴን መባ አቅርቤአለሁ፤

15 ስለዚህ አንተን ለመቀበል ወጣሁ፤ በብርቱም ፈለግኹህ፤ እነሆም አገኘሁህ!

16 ከግብጽ አገር የመጣውን ጌጠኛ አንሶላ በአልጋዬ ላይ አንጥፌአለሁ።

17 ከርቤ አልሙንና ቀረፋ ከተባሉት ቅመሞች የተሠራ ሽቶ አርከፍክፌበታለሁ።

18 ና ሌሊቱን ሙሉ በፍቅር እንርካ፤ በመተቃቀፍም ደስ ይበለን!

19 ባሌ በቤት የለም፤ ወደ ሩቅ አገር ሄዶአል፤

20 ብዙ ገንዘብ ይዞ ስለ ሄደ እስከ ሁለት ሳምንት አይመለስም።”

21 በሚማርኩ ቃሎችዋ አግባባችው፤ በለዘበ አነጋገርዋም አታለለችው።

22 በሬ ወደሚታረድበት ስፍራ እንደሚነዳ፥ አጋዘንም ቸኲሎ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ፥ ወዲያውኑ እርስዋን ተከትሎ ሄደ፤

23 ፍላጻም ሆድ ዕቃውን እንደሚወጋው ዐይነት ሆነ፤ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ ወፍ መሰለ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ሕይወቱ በአደጋ ላይ ለመውደቅ መቃረቡን አላወቀም።

24 እንግዲህ ልጄ ሆይ! አድምጠኝ፤ የምልህንም በጥንቃቄ ስማ፤

25 እንደዚህ ዐይነትዋ ሴት ልብህን እንድትማርክ አታድርጋት፤ የእርስዋንም መንገድ በመከተል አትሳሳት።

26 እርስዋ ለብዙ ሰዎች የመጥፊያ ምክንያት ሆናለች፤ እጅግ ብዙ ሰዎች በእርስዋ ተማርከው ጠፍተዋል።

27 ወደ እርስዋ ቤት የሚወስደው መንገድ ወደ ሞትና ወደ መቃብር የሚያወርድ ጐዳና ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos