Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ነህምያ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ነህምያ የገጠመውን የሥራ ተቃውሞ ሁሉ መቋቋሙ

1 እኛ አይሁድ የቅጽሩን ግንብ ሥራ መጀመራችንን ሰንባላጥ በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ ተበሳጭቶም ሊዘባበትብን ተነሣ።

2 በጓደኞቹና በሰማርያ ወታደሮች ፊት “እነዚህ ደካሞች አይሁድ ምን ለማድረግ አስበዋል? ከተማይቱን እንደገና መልሰው ለመሥራት ዐቅደዋልን? መሥዋዕት በማቅረብስ ሥራውን በአንድ ቀን ለመፈጸም የሚችሉ ይመስላቸዋልን? ለግንብ የሚሆኑ ድንጋዮችንስ ከተቃጠለው ፍርስራሽ ክምር ውስጥ ማውጣት ይችሉ ይሆን?” ሲል በመዘበት ተናገረ።

3 በአጠገቡም ቆሞ የነበረው ጦቢያ በበኩሉ፦ “እነርሱ ምን ዐይነት ቅጽር መሥራት ይችላሉ? የእነርሱ ግንብ ቀበሮ እንኳ ብትወጣበት ሊፈርስ ይችላል!” ሲል በማፌዝ ተናገረ።

4 እኔም እንዲህ ስል ጸለይሁ፤ “አምላክ ሆይ! እንዴት እንደሚሳለቁብን ተመልከት፤ ይህም ስድባቸው በራሳቸው ላይ ይምጣባቸው፤ ያላቸውን ሀብት ሁሉ ተገፈው በባዕድ አገር ስደተኞች ይሁኑ፤

5 ስለሚያደርጉት ክፉ ነገር ምሕረት አታድርግላቸው፤ የፈረሰውን በመሥራታችን በስድብ አዋርደውናልና በደላቸውን አትርሳ።”

6 እኛም ቅጽሩን መልሶ የማነጹን ሥራ ቀጠልን፤ ሕዝቡ በትጋት በመሥራቱ ሥራው እየተፋጠነ ሄዶ ግማሽ ደረሰ።

7 ሰንባላጥ፥ ጦቢያና የዐረብ፥ የዐሞን፥ የአሽዶድም ሕዝብ ጭምር የኢየሩሳሌምን ቅጽር ግንብ እንደገና መልሰን በመሥራት ረገድ ጥሩ የሥራ ውጤት ማስገኘታችንንና በቅጽሮቹ መካከል የነበሩት ክፍት ቦታዎች መዘጋታቸውን በሰሙ ጊዜ በብርቱ ተቈጡ፤

8 ስለዚህም በአንድነት ተባብረው ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣትና አደጋ ጥለው ሽብር ለመፍጠር በእኛ ላይ አድማ አደረጉ፤

9 እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ እነርሱንም ለመቋቋም ሌሊትና ቀን ቆመው የሚጠብቁ ዘበኞችን መደብን።

10 በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች “የሸክም ሥራ እያደከመን ሄደ፤ ገና መነሣት ያለበት ፍርስራሽ ብዙ ነው፤ ቅጽሩን እንሠራ ዘንድ አንችልም” አሉ።

11 “ጠላቶቻችን የምናደርገውን ከማወቃቸውና ከማየታቸው በፊት በመካከላቸው ተገኝተን እነርሱን ገድለን ሥራቸውንም እናቆመዋለን” አሉ።

12 በጠላቶቻችን መካከል የሚኖሩ አይሁድ ወደ ከተማው እየመጡ ጠላቶቻችን እኛን ለማጥቃት ያቀዱ መሆናቸውን ደጋግመው በማስጠንቀቅ ነገሩን።

13 ስለዚህም ከሕዝባችን መካከል ሰይፍ፥ ጦርና ቀስት የያዙ ሰዎችን በየጐሣቸው በማዘጋጀት፥ ሥራው ባልተጠናቀቀበት ቦታ ሁሉ በቅጽሩ ግንብ በስተጀርባ እንዲመሸጉ አደረግሁ።

14 ሕዝቡ ተጨንቀው ስላየሁ፥ እነርሱንና መሪዎቻቸውን፥ ሌሎችንም ባለሥልጣኖች ሁሉ “ከጠላቶቻችን የተነሣ አትፍሩ፤ ምን ያኽል ታላቅና ግርማው የሚያስፈራ አምላክ እንዳለንና እርሱ ስለ ወገኖቻችሁ፥ ስለ ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ ስለ ቤት ንብረታችሁም እንደሚዋጋላችሁ አስታውሱ” አልኳቸው።

15 ጠላቶቻችንም የተማማሉበትን አድማ የደረስንበት መሆኑን ሰሙ፤ እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን እንዳከሸፈባቸው ተገነዘቡ፤ ከዚያ በኋላ ሁላችንም የቅጽሩን ግንብ መሥራታችንን ቀጠልን።

16 ከዚህም ጊዜ ጀምሮ እኔ ያሰለፍኳቸው ሰዎች እኩሌቶቹ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ ጥሩር ለብሰው፥ ጦር ይዘው፥ ጋሻ አንግበው፥ ቀስት ደግነው ዘብ በመቆም እንዲጠብቁ አደረግሁ፤ መሪዎቻችንም ለሕዝቡ ሙሉ ድጋፍ ይሰጡ ነበር፤

17 ቅጽሩን የሚሠሩትን ሁሉ ያበረታቱ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ፥ ተሸካሚዎቹ ጭምር በአንድ እጃቸው ሲሠሩ፥ በሌላ እጃቸው የጦር መሣሪያ ይዘው ለመከላከል ዝግጁዎች ነበሩ።

18 እያንዳንዱም ግንበኛ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ እምቢልታ ነፊውም ከአጠገቤ አይለይም ነበር።

19 ሕዝቡን፥ መሪዎቻቸውንና ሹማምንቱን “የቅጽሩ ሥራ ታላቅና እጅግ ሰፊ ስለ ሆነ፥ እርስ በርሳችን በመራራቃችን አንዱ ከሌላው ጋር ለመገናኘት አይችልም።

20 የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ወደ እኔ መጥታችሁ በዙሪያዬ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋልናል” አልኳቸው፤

21 ስለዚህም በየቀኑ ከማለዳ ጀምሮ በምሽት፥ ከዋክብት እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ እኩሌቶቹ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ መሣሪያ ታጥቀው ዘብ በመቆም ይጠብቁ ነበር።

22 በዚህን ጊዜ የሥራ ኀላፊዎቹን “በሌሊት ከተማይቱን ለመጠበቅ፥ ቀን ሥራችንን ያለ ሥጋት ለመሥራት እንችል ዘንድ እናንተም ሆናችሁ ረዳቶቻችሁ፥ ሌሊት ሌሊት በኢየሩሳሌም ቈዩ” አልኳቸው።

23 እኔም ሆንኩ የሥራ ጓደኞቼ፥ አገልጋዮቼም ሆኑ የክብር ዘቦቼ፥ ሁላችንም ሌሊት እንኳ ልብሳችንን አናወልቅም ነበር። በዚህም ዐይነት ውሃ ስንቀዳ እንኳ መሣሪያችን ከእጃችን አልተለየም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos