Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሚክያስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ድኾችን የሚጨቊኑ ሰዎች የሚገጥማቸው መጥፎ ዕድል

1 ክፉ ሥራ ለመሥራት ለሚያቅዱና በመኝታቸው ሳሉ ተንኰል ለሚያውጠነጥኑ ወዮላቸው! ያን ለማድረግ ሥልጣን ስላላቸው ሌሊቱ ሲነጋ ዕቅዳቸውን በሥራ ላይ ያውሉታል።

2 የእርሻ ቦታ ሲፈልጉ የሌላውን ቀምተው ይወስዳሉ፤ ቤትም ሲፈልጉ ነጥቀው ይወስዳሉ፤ የሰውን መብት ረግጠው ሀብቱን ይዘርፋሉ።

3 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ በእናንተ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ፤ ከዚህም ልታመልጡ ፈጽሞ አትችሉም፤ ያ አሠቃቂ ጊዜ ስለሚሆን በትዕቢት መመላለስ አትችሉም።

4 በዚያን ቀን ሰዎች ያፌዙባችኋል፤ እንዲህም እያሉ የምፀት ሙሾ ያወርዱላችኋል፦ “እኛ ፈጽሞ ጠፍተናል! እግዚአብሔር የሕዝባችንን ንብረት ወሰደብን፤ ርስታችንንም ለማራኪዎቻችን አከፋፈለ።”

5 ምድሩ ተመልሶ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በሚሰጥበት ጊዜ እናንተ ምንም ድርሻ አይኖራችሁም።

6 የእነርሱ ነቢያት “ትንቢት አትናገር፤ እንደዚህ ያለው ውርደት የማይደርስብን ስለ ሆነ ስለ ነዚህ ጉዳዮች ትንቢት አትናገር” ይሉኛል።

7 ንግግራቸውንም በመቀጠል! “የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ይህ መባል አለበትን? የእግዚአብሔር ትዕግሥት አልቋልን? እነዚህስ የእርሱ ድርጊቶች ናቸውን?” ብለው ይጠይቃሉ፤ ለመሆኑ አካሄዳቸው ቀጥተኛ ለሆነ የእኔ ቃላት መልካም ነገር አያደርጉምን?

8 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል፦ “በሕዝቤ ላይ በጠላትነት ተነሥታችኋል፤ ከጦርነት ተመልሰው በመተማመን በመካከላችሁ የሚያልፉትን ሰላማዊ ሰዎች ገፈፋችሁ፤

9 በሕዝቤ መካከል ያሉትን ሴቶች ከመልካም ቤት ንብረታቸው አፈናቅላችሁ አሳደዳችሁ፤ ልጆቻቸውንም ከእኔ በረከትና ክብር ዘወትር እንዲለዩ አደረጋችሁ።

10 በርኲሰት ምክንያት አሠቃቂ ጥፋት የሚደርስ በመሆኑ በዚህ ማረፍ አይቻልም፤ ስለዚህ ተነሥታችሁ ሂዱ።

11 “አንድ ሰው ባዶ ቃላትን በመደርደር ስለ ወይንና ስለ ጠንካራ መጠጥ አስተምራችኋለሁ ቢላችሁ የዚህ ሕዝብ ነቢይ የሚሆነው እርሱ ነው።

12 “የእስራኤል ሕዝብ! በጎች በበረት፥ የበግ መንጋም በማሰማሪያ ቦታ እንደሚሰበሰብ በእርግጥ ከእስራኤል ሕዝብ የተረፉትን በአንድነት እሰበስባለሁ፤ ምድሪቱም በሕዝብ የተሞላች ትሆናለች” ይላል እግዚአብሔር።

13 መንገዱን በርግዶ በሚከፍትላቸው መሪ አማካይነት በተከፈተው ሰፊ በር ተግተልትለው ይወጣሉ፤ እግዚአብሔርም ንጉሣቸው በፊታቸው እየሄደ ይመራቸዋል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos