Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ባለ ማወቅ ስለ ተፈጸመ በደል የሚቀርብ መሥዋዕት

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ይህ ነው፦ ማንም ሰው ተሳስቶ ኃጢአት ቢሠራ ወይም ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ትእዛዞች አንዱን ቢተላለፍ ከዚህ የሚከተለውን ሥርዓት ይጠብቅ፦

3 “ተቀብቶ የተሾመው ካህን ኃጢአት ሠርቶ ሕዝቡን እንደ በደለኛ የሚያስቈጥር ሆኖ ቢገኝ፥ ምንም ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን ያምጣ፤ ስለ ኃጢአቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው።

4 ኰርማውንም ወደ ድንኳኑ ደጃፍ አምጥቶ እጁን በእንስሳው ራስ ላይ በመጫን በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይረደው።

5 ከዚያም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ከኰርማው ደም ጥቂት ወስዶ ወደ ድንኳኑ በማስገባት፥

6 በቤተ መቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሆኖ ደሙን በጣቱ እያጠቀሰ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው።

7 ከዚያም ደግሞ ጥቂት ደም ወስዶ በድንኳኑ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው አራት ማእዘን ጒጦች ላይ ያኑር፤ የተረፈውን ደም ግን በድንኳኑ መግቢያ በኩል የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፍስሰው።

8 ከዚህም ኰርማ ስቡን ሁሉ፥

9 ኲላሊቶቹን፥ እነርሱም የተሸፈኑበትን ስብና እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሸፈነው ስብ ምርጥ የሆነውን ይውሰድ።

10 ሊቀ ካህናቱም ይህን ስብ ሁሉ ተቀብሎ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው፤ አፈጻጸሙም ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው የእንስሳ ስብ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚያቀርበው ዐይነት ይሁን።

11 ነገር ግን ቆዳውን፥ ሥጋውን ሁሉ፥ ራሱንና እግሮቹን፥ አንጀቱንና የሆድ ዕቃውን በሙሉ፥

12 ከሰፈር ውጪ ያውጣ፤ ዐመድ ወደሚፈስበት ርኩስ ወዳልሆነ ስፍራ በመውሰድ እንጨት ሰብስቦ ያንድድና በእሳት ያቃጥለው።

13 “ባለማወቅ ኃጢአት የሠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ቢሆንና፥ ጉዳዩም ከማኅበረሰቡ ቢሰወር፥ ይህም ኃጢአት እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸው ትእዛዞች አንዱን በማፍረስ በደለኞች ቢያደርጋቸው፥

14 የተሠራው ኃጢአት እንደ ታወቀ ወዲያውኑ ማኅበሩ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ያምጣ፤ እርሱንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ያቅርቡት፤

15 የማኀበሩም አለቆች እጆቻቸውን በኰርማው ራስ ላይ ይጫኑበትና በዚያው በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይታረድ።

16 የተቀባው ካህንም ከኰርማው ደም ጥቂት ይዞ ወደ ድንኳኑ ይግባ፤

17 በቤተ መቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሆኖ ደሙን በጣቱ እያጠቀሰ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይርጨው።

18 ደግሞም ጥቂት ደም ወስዶ በድንኳኑ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ባለው በመሠዊያው ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚያም የተረፈውን ደም በድንኳኑ መግቢያ በኩል የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፍስሰው።

19 ከዚህም ቀጥሎ የዚህን ወይፈን ስብ ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው።

20 አፈጻጸሙም ለኃጢአት መሥዋዕት በሚቀርበው ኰርማ ላይ በሚደረገው ዐይነት ይሁን፤ በዚህም ዐይነት ስለ ሕዝቡ ኃጢአት መሥዋዕትን ያቀርባል፤ ሕዝቡም የኃጢአታቸውን ይቅርታ ያገኛሉ።

21 ከዚህም በኋላ ኰርማውን ከሰፈር ወደ ውጪ አውጥቶ ስለ ራሱ በደል በቀረበው ወይፈን ላይ እንደተፈጸመው ዐይነት ያቃጥለው፤ ይህም የማኅበረሰቡን ኃጢአት የሚያስወግድ መሥዋዕት ይሆናል።

22 “ኃጢአት የሠራውና ባለማወቅ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዘው ትእዛዝ በመተላለፍ በደለኛ የሆነው የሕዝብ መሪ ከሆነ፥

23 ኃጢአት መሥራቱን እንዳወቀ ወዲያውኑ ምንም ነውር የሌለበትን ተባዕት ፍየል የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ።

24 እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ጭኖ፥ ከመሠዊያው በስተ ሰሜን በኩል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይረደው፤ ይህም ኃጢአትን የሚያስወግድ መሥዋዕት ይሆናል።

25 ካህኑ የእንስሳውን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን ላይ በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህ የተረፈውንም በሚቃጠል መሥዋዕት በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው።

26 ስቡንም ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የዚህም አፈጻጸም ለአንድነት መሥዋዕት የቀረቡትን እንስሶች ስብ ባቃጠለው ዐይነት ይሁን፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለ ሕዝቡ መሪ ኃጢአት መሥዋዕት በማቅረብ ያስተሰርያል፤ መሪውም የኃጢአቱን ይቅርታ ያገኛል።

27 “ኃጢአት የሠራውና ባለማወቅም እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸው ትእዛዞች አንዱን የተላለፈውና በደለኛ የሆነው ሰው ከተራው ሕዝብ ወገን ከሆነ፥

28 ኃጢአት መሥራቱን እንዳወቀ ወዲያውኑ ምንም ነውር የሌለባት እንስት ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ያቅርብ።

29 እጁንም በእንስሳይቱ ራስ ላይ ይጫን፤ ከመሠዊያው በስተ ሰሜን ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይረዳት።

30 ካህኑም የእንስሳይቱን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው።

31 ለአንድነት መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን ስብ በመግፈፍ በሚፈጽመው ዐይነት የዚህችንም እንስሳ ስብ ሁሉ ገፎ ያስወግድ፤ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህ ዐይነት ካህኑ ስለዚያ ሰው የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ያቀርባል፤ ያም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።

32 “ሰውየው ስለ ኃጢአቱ ስርየት የበግ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ ምንም ነውር የሌለባት እንስት ትሁን።

33 እርሱም በእንስሳይቱ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ ከመሠዊያው በስተሰሜን በኩል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይረዳት፤

34 ካህኑም የእንስሳይቱን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው፤

35 ከዚህም በኋላ ለአንድነት መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን ስብ በመግፈፍ በሚፈጽመው ዐይነት የዚህችንም እንስሳ ስብ ሁሉ ገፎ ያስወግድ፤ እርሱንም ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የምግብ መባ ጋር በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለዚያ ሰው የኃጢአት መሥዋዕትን በማቅረብ ያስተስርይለት፤ ያም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos