ዘሌዋውያን 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእህል መባ 1 ማነኛውም ሰው ለእግዚአብሔር የእህል መባ በሚያቀርብበት ጊዜ ምርጥ ዱቄት መሆን አለበት፤ በእርሱም ላይ የወይራ ዘይትና ዕጣን ይጨምርበት፤ 2 የአሮን ዘር ወደ ሆኑት ካህናት ያምጣው፤ ተረኛው ካህን ከዚያ ዱቄት በእፍኙ ሙሉ በመዝገን ዘይቱንና ዕጣኑን በሙሉ ወስዶ ለእግዚአብሔር የቀረበ መሆኑን ለማሳወቅ በመሠዊያው ላይ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም ዐይነቱ የምግብ መባ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 3 ከእህል መባውም የተረፈው ዱቄት የአሮን ዘር ለሆኑት ካህናት ይሰጥ፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ከቀረበው መባ የሚቃጠል ቊርባን በመሆኑ እጅግ የተቀደሰ ነው። 4 መባው በምድጃ የተጋገረ ከሆነም እርሾ ያልነካው ይሁን፤ እርሱም የወይራ ዘይት ተደባልቆበት ከላመ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ ወይም በዘይት የታሸ ቂጣ መሆን አለበት። 5 መባው በምጣድ የተጋገረ ኅብስት ከሆነ እርሾ ሳይነካው የወይራ ዘይት ተጨምሮበት ከላመ ዱቄት የተዘጋጀ ይሁን፤ 6 ኅብስቱንም ቈራርሰህ በእርሱ ላይ የወይራ ዘይት ታፈስበትና የእህል መባ አድርገህ ታቀርበዋለህ። 7 መባው በመጥበሻ የተጋገረ ቂጣ ከሆነ የወይራ ዘይት ተጨምሮበት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጀ ይሁን። 8 የእህሉንም መባ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ መሥዋዕት አድርገህ ለካህኑ ታስረክበዋለህ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል። 9 ካህኑም ከዚያ መባ ከፊሉን ወስዶ በሙሉ ለእግዚአብሔር የቀረበ መሆኑን ለማስታወስ በመሠዊያው ላይ በሚገኘው እሳት ያቃጥለዋል፤ ይህም ዐይነት በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 10 ቀሪው መባ ግን ለካህናቱ ይሰጥ፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ከቀረበው መባ ተከፍሎ የተወሰደ በመሆኑ እጅግ የተቀደሰ ነው። 11 የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው መባ ጋር የሚገኘውን እርሾም ሆነ ማር. በእሳት ማቃጠል ስለሌለብህ፥ ለእግዚአብሔር የምታቀርበው የእህል መባ ሁሉ ምንም ዐይነት እርሾ ያልነካው ይሁን፤ 12 በየዓመቱ የመከር መጀመሪያ ከእህላችሁ በኲራት አድርጋችሁ የምታቀርቡትንም መባ ለእግዚአብሔር ታመጣላችሁ፤ እርሱ ግን በመሠዊያው ላይ አይቃጠል። 13 ይህ የእህል ቊርባን ስለ ሆነ በእህል ቊርባንህ ሁሉ ላይ ጨው ጨምርበት፤ የአምላክህን የጨው ቃል ኪዳን አትተው፤ በቊርባኖች ሁሉ ጨው መግባት አለበት። 14 የመከር ወራት መጀመሪያ የሆነውን በኲራት በምታቀርብበትም ጊዜ ተጠብሶ የታሸ እሸት ይሁን። 15 ይህ የእህል መባ ስለ ሆነ በእርሱ ላይ የወይራ ዘይትና ዕጣን ጨምርበት፤ 16 ካህኑም ከዚያ መባ ከፊሉን ወስዶ ለእግዚአብሔር የቀረበ መሆኑን ለማስታወስ ዘይቱንም፥ ዕጣኑንም በሙሉ ከእህሉ ጋር አብሮ ያቃጥለዋል። |