ኤርምያስ 41 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 በዚሁ ዓመት በሰባተኛው ወር ከንጉሡ ታላላቅ ባለ ሥልጣኖች አንዱ፥ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል የሆነውና የኤሊሻማዕ የልጅ ልጅ የነታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ሆኖ አገረ ገዢውን ገዳልያን ለመጐብኘት ወደ ምጽጳ ሄደ፤ ሁሉም በማዕድ ተቀምጠው አብረው ምግብ እየተመገቡ ሳሉ፥ 2 እስማኤልና ዐሥሩ ሰዎች የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ላይ የሾመውን ገዳልያን በሰይፍ ገደሉት። 3 እስማኤል በምጽጳ ከገዳልያ ጋር የነበሩትን አይሁድንና በዚያ ተገኝተው የነበሩትን የባቢሎናውያንን ወታደሮች ጭምር ፈጀ። 4 በማግስቱም ገዳልያ መሞቱን ማንም ሳያውቅ፥ 5 ከሴኬም፥ ከሴሎና ከሰማርያ ሰማኒያ ሰዎች በድንገት መጡ፤ እነርሱም በሐዘን ጢማቸውን ላጭተው፥ ልብሳቸውን ቀደው፥ ፊታቸውን ነጭተው ነበር፤ ለቤተ መቅደስም መባ የሚያቀርቡትን እህልና ዕጣን ይዘው ነበር፤ 6 ስለዚህም እስማኤል ከምጽጳ እያለቀሰ ሊቀበላቸው ወጣ፤ ወደ እነርሱም በቀረበ ጊዜ “የአሒቃም ልጅ ወደ ሆነው ወደ ገዳልያ ኑ” አላቸው። 7 እነዚያም ሰዎች ከተማይቱ ውስጥ እንደ ገቡ የናታልያ ልጅ እስማኤልና ተከታዮቹ ገድለው ጒድጓድ ውስጥ ጣሉአቸው። 8 ከእነዚያ ሰማኒያ ሰዎች መካከል በተለይ ዐሥሩ ሰዎች “እባክህ አትግደለን! እኛ በእርሻ ውስጥ የደበቅነው ብዙ ስንዴ፥ ገብስ፥ የወይራ ዘይትና ማር. አለን” ብለው እስማኤልን ለመኑት። እርሱም ምሕረት አደረገላቸው። 9 እነዚያን ሰዎች ገድሎ የጣለበትም ያ ጒድጓድ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ አደጋ በጣለበት ጊዜ ንጉሥ አሳ ለመጠባበቂያ አስቈፍሮት የነበረ ትልቅ ጒድጓድ ነበር፤ እስማኤል ያን ጒድጓድ በሬሳ ሞላው። 10 ከዚያም በኋላ የንጉሡን ሴቶች ልጆችና የቀሩትንም ሕዝብ በምጽጳ አሰረ፤ እነዚህም ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ ጦር አዛዥ ናቡዛርዳን በገዳልያ ሥር እንዲጠበቁ ዐደራ የተሰጡ ነበሩ፤ እስማኤል ግን እነዚህን ሁሉ ማርኮ ወደ ዐሞን ግዛት አቅጣጫ ተሻገረ። 11 ዮሐናንና ከእርሱ ጋር የነበሩት የሠራዊት መሪዎች ሁሉ እስማኤል የፈጸመውን ወንጀል ሰሙ፤ 12 ስለዚህም ከሰዎቻቸው ሁሉ ጋር አሳደው ገባዖን ውስጥ ባለው ታላቅ ኲሬ አጠገብ ደረሱበት። 13 እስማኤል አስሮ የወሰዳቸው ሁሉ ዮሐናንንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊቱን መሪዎች ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14 መለስ ብለውም በመሮጥ ከእነርሱ ጋር ተደባለቁ፤ 15 እስማኤልና ስምንት ሰዎቹ ግን ከዮሐናን እጅ አምልጠው ወደ ዐሞን ምድር ኰበለሉ። 16 ከዚህ በኋላ ዮሐናንና ከእርሱ ጋር ያሉት የሠራዊቱ መሪዎች፥ እስማኤል ገዳልያን ከገደለ በኋላ ከምጽጳ ማርኮ የወሰዳቸውን ወታደሮች፥ ሴቶች፥ ሕፃናትና ጃንደረቦች ሁሉ መለሱ። 17-18 እነርሱም የባቢሎን ንጉሥ ገዢ አድርጎ የሾመውን ገዳልያንን እስማኤል ስለ ገደለው ባቢሎናውያን አደጋ ያደርሱብናል ብለው ፈርተው ነበር፤ ስለዚህም ከባቢሎናውያን ፊት ሸሽተው ወደ ግብጽ ለመኰብለል ተነሡ፤ በቤተልሔም አጠገብ ባለችው ጌሩት ኪምሀም ተብላ በምትጠራው ቦታ ዕረፍት አደረጉ። |