Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጣኦት አምላኪዋ እስራኤል ፍርድ

1 የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርባቸው፤

3 እንዲህም በል፦ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮች፥ ለኮረብቶች፥ ለምንጮችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ።

4 መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፥ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሠበራሉ፥ የተገደሉ ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ።

5 የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፥ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።

6 በምትኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ከተሞቹ ይፈርሳሉ፥ የኮረብታው መስገጃዎችም ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፥ መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ ባድማም ይሆናሉ፥ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ ያልቃሉም፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይቆረጣሉ፥ ሥራችሁም ይሻራል።

7 የተገደሉትም በመካከላችሁ ይወድቃሉ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

8 ነገር ግን በአገሮች መካከል በተበተናችሁ ጊዜ የተወሰኑትን በአሕዛብ መካከል ከሰይፍ በሕይወት አስቀርላችኋለሁ።

9 ያመለጡት ተማርከው በሄዱባቸው በአሕዛብ መካከል ሆነው ያስታውሱኛል፤ ምክንያቱም ከእኔ በራቀው አመንዝራ ልባቸውና፥ ጣዖቶቻቸውን በተከተሉ በአመንዝራ ዐይኖቻቸው ተሰብሬአለሁና፥ በክፉ ስራቸውና በርኩሰታቸውም ሁሉ ራሳቸውን ይጸየፋሉ።

10 እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ ይህን ክፉ ነገር እንደማመጣባቸው መናገሬ በከንቱ አይደለም።

11 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእጅህ አጨብጭብ፥ በእግርህም እየረገጥህ፥ ስለ የእስራኤል ቤት ክፉ የርኩሰት ሥራዎቻቸው ሁሉ ወዮ! በል፤ በሰይፍ፥ በራብና በቸነፈር ይወድቃሉና፤

12 በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፥ በቅርብ ያለውም በሰይፍ ይወድቃል፥ በሕይወት የተረፈውና የዳነውም በራብ ይሞታል፥ መዓቴን በእነርሱ ላይ እፈጽማለሁ።

13 ሬሳዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፥ በረዣዥም ኮረብታ ሁሉ፥ በተራሮችም ራሶች ሁሉ፥ ከለመለመውም ዛፍ ሁሉ ሥርና ቅጠሉም ከበዛ ባሉጥ ሁሉ ሥር ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ባቀረቡበት ስፍራ በወደቁ ጊዜ ያኔ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

14 እጄንም በእነሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዲብላ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos