በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር።
መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁን፤ የእግዚአብሔር መልአክ ያባርራቸው።
በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለም፣ የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ።
የተበተኑትን እስራኤል የሚሰበስብ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከተሰበሰቡት በተጨማሪ፣ ሌሎችን እንደ ገና እሰበስባለሁ።”
“የተተውሽና የተጠላሽ፣ ማንም ሰው የማያልፍብሽ ብትሆኝም እንኳ፣ እኔ የዘላለም ትምክሕት፣ የትውልድም ሁሉ ደስታ አደርግሻለሁ።
ዘሮቻቸው በመንግሥታት፣ ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ፤ የሚያዩአቸውም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የባረካቸው ሕዝብ እንደ ሆኑ ያውቃሉ።”
እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር የተቤዣቸው ተብለው ይጠራሉ፤ አንቺም የምትፈለግ፣ ከእንግዲህም የማትተው ከተማ ትባያለሽ።
ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት፣ የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ዕረፍት አትስጡት።
“እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤
“የመንጋዬንም ቅሬታ ካባረርሁባቸው አገሮች ሁሉ እኔ ራሴ ሰብስቤ፣ ወደ መሰማሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ይበዛሉም።
እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከምርኮም እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”
እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።”
ይህች ከተማ፣ ለርሷ ያደረግሁትን በጎ ነገር ሁሉ በሚሰሙት የምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት ለዝና፣ ለደስታ፣ ለምስጋናና ለክብር ትሆናለች፤ ከምሰጣትም የተትረፈረፈ ብልጽግናና ሰላም የተነሣ ይፈራሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም።’
“ ‘ነገር ግን የሰዶምንና የሴት ልጆቿን፣ እንዲሁም የሰማርያንና የሴት ልጆቿን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የአንቺንም ምርኮ የእነርሱን በምመልስበት ጊዜ እመልሳለሁ።
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤልን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች መካከል በምሰበስብበት ጊዜ፣ አሕዛብ እያዩ ቅድስናዬን በመካከላቸው እገልጣለሁ፤ ከዚያም በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ፤ ይህም ለባሪያዬ ለያዕቆብ የሰጠሁት ነው።
የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።
ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ።
እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው አሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየስፍራው ሰብስቤ ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ይቀብሯቸዋል፤ እኔ የምከብርበትም ዕለት የመታሰቢያ ቀን ይሆናቸዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
በአሕዛብ መካከል እንዲሰደዱ ባደርግም፣ አንድም ሳላስቀር ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
“በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ ስመልስ፣
የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ። “እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ። የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤ አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።
“ያዕቆብ ሆይ፤ በርግጥ ሁላችሁንም እሰበስባለሁ፤ የእስራኤልንም ትሩፍ በአንድነት አመጣለሁ፤ በጕረኖ ውስጥ እንዳሉ በጎች በመሰማሪያ ላይ እንዳለ መንጋ በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ቦታውም በሕዝብ ይሞላል።
የሽባዎችን ትሩፍ፣ የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤ ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
ይህም ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሰጣል፤ እነርሱም በዚያ መሰማሪያ ያገኛሉ። በአስቀሎና ቤቶች ውስጥም በምሽት ይተኛሉ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋል፤ ምርኳቸውንም ይመልስላቸዋል።
በዚያ ጊዜ፣ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ ዐንካሶችን እታደጋለሁ፤ የተበተኑትንም እሰበስባለሁ፤ በተዋረዱበት ምድር ሁሉ፣ ለውዳሴና ለክብር አደርጋቸዋለሁ።
የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል የርግማን ምሳሌ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ። አትፍሩ፤ ነገር ግን እጃችሁን አበርቱ።”
በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በጽድቅና በታማኝነት አምላካቸው እሆናለሁ።”
“ከዚያም በኋላ የተድላ ምድር ስለምትሆኑ፣ ሕዝቦች ሁሉ የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት አንተ፣ ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፣ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ በዛሬው ዕለት ተናግሯል።
ከፈጠራቸው ሕዝቦች ሁሉ በላይ በምስጋና፣ በስም፣ በክብርም ከፍ እንደሚያደርግህና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ እንደምትሆን ተናግሯል።