ለዐመፀኛዪቱና ለረከሰች፣ ለጨቋኞች ከተማ ወዮላት!
ስለዚህ፣ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ “ይህን ቃል ስላቃለላችሁ፣ ግፍን ስለ ታመናችሁ፣ ማታለልን ስለ ተደገፋችሁ፣
የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የወይን ቦታው የእስራኤል ቤት ነው፤ የይሁዳ ሰዎችም የደስታው አትክልት ናቸው። ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤ ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።
በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀናል፤ ሐሰት ተናግረናል፤ አምላካችንን ከመከተል ዘወር ብለናል፤ ዐመፃንና ግፍን አውርተናል፤ ልባችን የፀነሰውን ውሸት ተናግረናል።
ድሮቻቸው ልብስ አይሆኑም፤ በሚሠሩትም ሰውነታቸውን መሸፈን አይችሉም፤ ሥራቸው ክፉ ነው፤ እጃቸውም በዐመፅ ሥራ የተሞላ ነው።
“የአንተ ዐይንና ልብ ያረፉት ግን፣ አጭበርብሮ ጥቅምን በማግኘት፣ የንጹሑን ደም በማፍሰስ፣ ጭቈናንና ግፍን በመሥራት ላይ ብቻ ነው።”
ይህ ሕዝብ ግን የሸፈተና እልኸኛ ልብ አለው፤ መንገድ ለቅቆ ሄዷል፤
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ዛፎቹን ቍረጡ፤ በኢየሩሳሌም ዙሪያ የዐፈር ድልድል ሥሩ። ይህች ከተማ ቅጣት ይገባታል፤ ግፍን ተሞልታለችና።
የውሃ ጕድጓድ ውሃ እንደሚያመነጭ፣ እርሷም እንዲሁ ክፋቷን ታፈልቃለች። ዐመፅና ጥፋት በውስጧ ይስተጋባል፤ ሕመሟና ቍስሏ ዘወትር ይታየኛል።
በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጕደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቍናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል።
አባቶችና እናቶች በውስጥሽ ተዋረዱ፤ መጻተኞች ተጨቈኑ፤ ድኻ አደጎችና መበለቶች ተንገላቱ።
ይህን አምጥተውብሻል፤ ከአሕዛብ ጋራ በማመንዘር በጣዖቶቻቸው ረክሰሻልና።
ከሆድ ዕቃውም ጥሬ ቤቱን ለይቶ ከላባዎቹ ጋራ ከመሠዊያው በስተምሥራቅ በኩል፣ ዐመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይጣለው።
ለአዛጦን ምሽግ፣ ለግብጽም ምሽግ እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፤ “በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፤ በውስጧ ያለውን ታላቅ ሁከት፣ በሕዝቧም መካከል ያለውን ግፍ እዩ።”
እናንተ በሰማርያ ተራራ የምትኖሩ የባሳን ላሞች፤ ድኾችን የምትጨቍኑና ችግረኞችን የምታስጨንቁ፣ ባሎቻችሁንም፣ “መጠጥ አቅርቡልን” የምትሉ ሴቶች ይህን ቃል ስሙ፤
ዕርሻ ይመኛሉ፤ ይይዙታልም፤ ቤት ይመኛሉ፤ ይወስዱታልም፤ የሰውን ቤት፣ የባልንጀራን ርስት አታልለው ይወስዳሉ።
መበለቲቱን ወይም ድኻ አደጉን፣ መጻተኛውን ወይም ድኻውን አታስጨንቁ፤ በልባችሁም አንዳችሁ በአንዳችሁ ላይ ክፉ አታስቡ።’
“ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።