በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም።” መላዪቱ ምድር፣ በቅናቱ ትበላለች፤ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ፣ ድንገተኛ ፍጻሜ ያመጣባቸዋልና።
ስለዚህም እግዚአብሔር፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ።
ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ከአባቶቻቸው ይልቅ እነርሱ በሠሩት ኀጢአት ይበልጥ የቅናት ቍጣውን አነሣሡ፤
ክፉ ሰው በመቅሠፍት ቀን እንደሚጠበቅ፣ በቍጣም ቀን እንደሚተርፍ አታውቁምን?
ቤታቸውን በብር ከሞሉ፣ ወርቅም ከነበራቸው ገዦች ጋራ ባረፍሁ ነበር።
በኰረብታ ማምለኪያዎቻቸው አስቈጡት፤ ተቀርጸው በተሠሩ ጣዖቶቻቸው አስቀኑት።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ነው? የምትቈጣውስ ለዘላለም ነውን? ቅናትህስ እንደ እሳት ሲነድድ ይኖራልን?
በቍጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች።
የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ እንደማይወጣ ረዥም ግንብም ይቈጥሩታል።
ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የእስራኤል ኀያል እንዲህ ይላል፤ “ወዮ! በባላንጣዎቼ ላይ ቍጣዬን እገልጣለሁ፤ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ።
የእስራኤል ብርሃን እሳት፣ ቅዱሱም ነበልባል ይሆናል፤ በአንድ ቀንም እሾኹንና ኵርንችቱን እሳት ይበላዋል፤
በምትጐበኙበት ቀን ምን ይውጣችኋል? ጥፋት ከሩቅ ሲመጣስ ምን ትሆናላችሁ? ርዳታን ለማግኘትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ሀብታችሁንስ የት ታገኙታላችሁ?
“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ በሰውና በእንስሳ ላይ፣ በዱር ዛፍና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፤ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።
የደስታና የተድላን ድምፅ፣ የሙሽራና የሙሽራዪቱን ድምፅ ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም መንገዶች አጠፋለሁ፤ ምድሪቱ ባድማ ትሆናለችና።
“ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣ የቀበሮም ጐሬ አደርጋታለሁ፤ የይሁዳንም ከተሞች፣ ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
ለአመንዝራና ለነፍሰ ገዳይ ሴቶች የሚገባውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፤ በመዓቴና በቅናቴ እስከ ደም እበቀልሻለሁ።
የቅናት ቍጣዬን በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ እነርሱም በአንቺ ላይ በቍጣ ይወጣሉ፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቈርጣሉ፤ ከአንቺ ወገን የተረፉትም በሰይፍ ይወድቃሉ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዱብሻል፤ የተረፉትንም እሳት ይበላቸዋል።
ዐመፅ ዐድጋ የክፋት በትር ሆነች፤ ከሕዝቡ አንድም አይተርፍም፤ ከሰዎቹ፣ ከሀብታቸውና እርባና ካለው ነገር አንዳች አይቀርም።
“ ‘ብራቸውን በየጐዳናው ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ርኩስ ነገር ይቈጠራል። በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ በኀጢአት እንዲወድቁ ዕንቅፋት ሆኖባቸዋልና በልተው አይጠግቡበትም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉበትም።
“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘መዓት! ተሰምቶ የማይታወቅ መዓት ይመጣል።
እናንተ በመክቴሽ ገበያ የምትኖሩ ዋይ በሉ፤ ነጋዴዎቻችሁ ሁሉ ይደመሰሳሉ፤ በብር የሚነግዱትም ሁሉ ይሞታሉ።
ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የሁከትና የጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል፤
የተወሰነው ጊዜ ሳይደርስ፣ ቀኑ እንደ ገለባ ሳይጠራርጋችሁ፣ የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ በእናንተ ላይ ሳይመጣ፣ የእግዚአብሔር የመዓት ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለዚህ እስከምፈርድበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፤ አሕዛብን ላከማች፣ መንግሥታትን ልሰበስብ፣ መዓቴንና ጽኑ ቍጣዬን በላያቸው ላፈስስ ወስኛለሁ። በቅናቴ ቍጣ እሳት፣ መላዋ ምድር ትቃጠላለችና።
ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?
ጌታን እናስቀናውን? በብርታትስ ከርሱ እንበልጣለንን?
በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን ከእኛ ጋራ ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ።