ልታደርጓቸው የሚገባችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባያችሁም እውነትንና ትክክለኛ ፍርድን አስፍኑ፤
አካሄዱ የቀና፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር፤
የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።
ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል።
እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው።
ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።
በዐራጣ አያበድርም፣ ከፍተኛ ወለድም አይቀበልም። እጁን ከበደል ይሰበስባል፤ በሰውና በሰው መካከል በትክክል ይፈርዳል።
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
“ ‘አትስረቁ። “ ‘አትዋሹ። “ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታልል።
ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤ በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤ ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር፣ ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።
ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።
ባለጠጎቿ ግፈኞች፣ ሰዎቿ ሐሰተኞች ናቸው፤ ምላሳቸውም አታላይ ናት።
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
የእስራኤል ቅሬታዎች ኀጢአት አይሠሩም፤ ሐሰትም አይናገሩም፤ በአንደበታቸውም ተንኰል አይገኝም። ይበላሉ፤ ይተኛሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።”
“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እውነተኛ ፍትሕ አስፍኑ፣ እርስ በርሳችሁ ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የአራተኛው፣ የአምስተኛው፣ የሰባተኛውና የዐሥረኛው ወር ጾሞች ለይሁዳ ቤት የደስታ፣ የተድላና የሐሤት በዓላት ይሆናሉ፤ ስለዚህ እውነትንና ሰላምን ውደዱ።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ ጽዮን እመለሳለሁ፤ በኢየሩሳሌም እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ተራራም ቅዱስ ተራራ ይባላል።”
ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና።
ስለዚህ ይህን እነግራችኋለሁ፤ በጌታም ዐደራ እላለሁ፤ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ልትመላለሱ አይገባም።
ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋራ እውነትን ተነጋገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነንና።
በዚህም ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን አያታልል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ እንደ እነዚህ ያለውን ኀጢአት ሁሉ የሚፈጽሙትን ይበቀላል፤
ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”