ትበሉና ትጠጡ የነበረውስ ለራሳችሁ አይደለምን?
በዚያችም ዕለት በእግዚአብሔር ፊት በታላቅ ደስታ በሉ፤ ጠጡም። ከዚያም የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ዐወቁ፤ ገዥ እንዲሆንም በእግዚአብሔር ፊት ቀቡት፤ ሳዶቅንም ካህናቸው እንዲሆን ቀቡት።
ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎች አላመጣህልኝም፤ በመሥዋዕትህም አላከበርኸኝም። በእህል ቍርባን እንድታገለግለኝ አላስቸገርሁህም፤ በዕጣን መሥዋዕትም አላሰለቸሁህም።
‘አንተ ካልተቀበልኸው፣ ስለ ምን ብለን ጾምን? አንተ ከጕዳይ ካልቈጠርኸው፣ ስለ ምን ራሳችንን አዋረድን?’ ይላሉ። “ሆኖም በጾማችሁ ቀን የልባችሁን ታደርጋላችሁ፤ ሠራተኞቻችሁንም ትበዘብዛላችሁ።
ለእኔ የሚገባውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሥጋውንም ይበላሉ፤ እግዚአብሔር ግን በእነርሱ አልተደሰተም፤ ስለዚህ ክፋታቸውን ያስታውሳል፤ ኀጢአታቸውን ይቀጣል፤ ወደ ግብጽም ይመለሳሉ።
የወይን ጠጅን ቍርባን ለእግዚአብሔር አያፈስሱም፤ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሠኘውም፤ እንዲህ ዐይነቱ መሥዋዕት ለእነርሱ የሐዘንተኞች እንጀራ ይሆንባቸዋል፤ የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ። ይህ ምግብ ለገዛ ራሳቸው ይሆናል፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ አይገባም።
“የምድሩን ሕዝብ ሁሉና ካህናቱን እንዲህ በላቸው፤ ‘ባለፉት ሰባ ዓመታት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር የጾማችሁትና ያዘናችሁት በርግጥ ለእኔ ነበርን?
ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች በሰላምና በብልጽግና ላይ ሳሉ፣ የደቡብና የምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ የሰው መኖሪያም በነበሩበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት የተናገረው ቃል ይህ አልነበረምን?’ ”
እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።
በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።
በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ፣ ማለትም የቀንድ ከብት፣ በግ፣ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተ ሰብህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በዚያ ትበላላችሁ፤ ሐሤትም ታደርጋላችሁ።
በርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።